
በኢንተርናሽናል ፈርትላይዘር ዴቨሎፕመንት ሴንተር ትራንስፎርም መርሐግብር የአማራ ክልልን የአፈር ጤንነት እና ለምነት ለመጠበቅ ያለመ ውይይት ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ፣ ከክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ ከአማራ ክልል ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት፣ ከግብርና ሚኒስቴር እና በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የባለ ድርሻ አካላት የውይይት መድረክ አቋቁሟል።
የግብርና ሚኒስትር የተፈጥሮ ሀብት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ማሞ ደግሶ እንደተናገሩት በአፈር አያያዝ ችግር ምክንያት የግብርና ምርት እና ምርታማነት በእጅጉ እየቀነሰ እንዲመጣ አድርጓል። በዚሀም የምግብ ዋስትና ችግር እንዲፈጠር ምክንያት ኾኗል።
እንደ ሀገር ከሚታረሰው መሬት 7 ነጥብ 2 ሚሊዮን ወይም 43 በመቶ በአሲዳማነት የተጠቃ ነው፤ ከዚህም 11 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በጨዋማነት የተጠቃ ነው ብለዋል። ችግሩን ለመከላከል ከ83 ሺህ በላይ ሄክታር መሬትን በግብርና ኖራ የማከም ሥራዎች በመሥራት የአፈር ለምነት እና ጤንነትን ለመጠበቅ መሠራቱን ገልጸዋል።
የተመዘገቡ ውጤቶች የሚበረታቱ ቢኾንም ዘላቂ የኾኑ የአፈር ልማት ጥበቃ ስልቶችን መተግበር እና በቴክኖሎጂ የታገዘ የግብርና አሠራርን መከተል አስፈላጊ ነውም ብለዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኅላፊ መሠሉ ብርሃኑ በክልሉ አምራች በኾኑ አካባቢዎች ከፍተኛ የአፈር አሲዳማነት ይስተዋላል ብለዋል። ይህም ምርታማነት ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ይፈጥራል ነው ያሉት። በእነዚህ አካባቢዎች መሬትን በኖራ የማከም እና የተቀናጀ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ነው የተናገሩት።
ትራንስ ፎርም የአፈር ጤንነት እና ለምነት መርሐግብር የኢትዮጰያ ፕሮግራም ዳይሬክተር ካሳሁን አዴሎ (ዶ.ር) በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች የአፈር ጤንነት ችግርን በመከላከል የአፈር ለምነትን ለማሻሻል እና ምርታማነትን ለማሳደግ ባለፈው አንድ ዓመት ጀምሮ ሢሠሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
እንደ ሀገር በአራት ዓመት ውስጥ 65ሺህ ሄክታር መሬት የአፈር ጤንነትን ለማሻሻል እና ለማገገም ዕቅድ ይዞ ተግባራዊ እያደረገ መኾኑንም አንስተዋል።
በአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአፈር እና ውኃ ምርምር ዳይሬክተር ተስፋዬ ፈይሳ (ዶ.ር) በክልሉ ከሚታረሰው መሬት ውስጥ 36 በመቶ የሚኾነው በአሲዳማ አፈር የተጠቃ ነው ብለዋል። ይህንን ለማከም አርሶ አደሮች የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ እንዲጠቀሙ እየተደረገ ይገኛልም ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
