
በዞኑ “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ሀሳብ ዞናዊ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በደጀን ወረዳ የትኖራ ቀበሌ ተጀምሯል። ።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ደረጀ ማንደፍሮ ባለፉት ዓመታት በተሠራው የአፈርና ውኃ ጥበቃ እና የአረንጓዴ አሻራ ተግባራት የደን ሽፋንን ከነበረበት 14 ነጥብ 6 በመቶ ወደ 18 ነጥብ 9 በመቶ ማድረስ እንደተቻለ ገልጸዋል። የጽድቀት ምጣኔን ከ71 በመቶ ወደ 81 በመቶ ማሳደግ እንደተቻለም አንስተዋል።
በዚህ ዓመትም ለተከላ ከተለዩ ከ261 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ላይ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች ለመትከል ወደ ተግባር መገባቱን ጠቁመዋል።
በአካባቢው ያለውን ጸጋ በአግባቡ በመጠቀም የፍራፍሬ ችግኞች ላይ በማተኮር ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ ዋለ አባተ የአየር ንብረት መዛባት ሊያስከትል የሚችለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ችግኞችን መትከል እና መንከባከብ የሕልውና ጉዳይ መኾኑን ገልጸዋል።
የተተከሉ ችግኞች ለፍሬ እንዲበቁ ያልተቋረጠ ክትትል እና እንክብካቤ ማድረገ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ኅብረተሰቡ ባለፉት ዓመታት በሰላም እጦት ምክንያት ከደረሰበት ጉዳት በመማር የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም በማጽናት ልማትን ማፋጠን እና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መትጋት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የምስራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ጥላሁን ንጋቱ በዞኑ ለተካላ ከተለዬ 33 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ከ260 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል።
አሳሳቢ እየኾነ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ እና የተፈጥሮ ሀብት መመናመንን ለመቀልበስ የአረንጓዴ አሻራ ተግባርን በልዩ ትኩረት አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ነው ያሉት።
ለአሚኮ አስተያየታቸውን የሰጡት የየትኖራ ቀበሌ አርሶ አደሮች ከዚህ በፊት ተፋሰሶችን በተለያዩ ችግኞች በመሸፈን አካባቢያቸውን ከመራቆት መታደጋቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም የተከሏቸውን የአትክልት እና ፍራፍሬ ችግኞች በመንከባከብ ለፍሬ ለማብቃት እና የደን
ሽፋንን ለማሳደግ እንደሚሠሩ ነው የገለጹት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
