
ዝክረ ሐምሌ 5/2008 ዓ.ም አሥረኛ ዓመት “ሐምሌ አምስት፣ የማይታጠፍ ቃል የማይፈታ ትጥቅ በሚል መሪ መልዕክት” በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን፤ በሁመራ ከተማ ተከብሯል።
ሐምሌ 5/2008 ዓ.ም የሕወሃት ቡድን የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት እና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ ሠብሣቢውን ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን ከጎንደር አፍኖ ለመውሰድ ያደረገው ሙከራ የከሸፈበት ቀን ነው።
ከዚያ ጊዜ በኋላ አድማሱን ባሰፋው ሕዝባዊ ትግል ሀገራዊ ለውጡ መምጣቱን ተከትሎ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብም ከሕወሃት አገዛዝ ነጻ መውጣቱን የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው ገልጸዋል።
በዕለቱ የሕወሃት ቡድን ቤታቸውን ከቦ የኀይል እርምጃ ለመውሰድ ሲሞክር ራሳቸውን ለትግሉ አሳልፈው በመስጠት ትግሉን ትውልድ እንዲያስቀጥለው በማሰብ እስከመጨረሻው መፋለማቸውን ደግሞ የዞኑ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ አስታውሰዋል።
ሐምሌ አምስት በጠንካራ የትግል መንፈስ የተገኘ ድል መኾኑን ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህሩ ዳኛቸው አሰፋ (ዶ.ር) አመላክተዋል።
ሐምሌ አምስት ላይ በነበረው ትግል የተሳተፉት ኮማንደር ደጀኔ ማሩ በዕለቱ የተደረገው ትግል ጀግንነት የታየበት መኾኑን ገልጸው የኮሎኔል ደመቀን ከበባ ለመስበር ከሶሮቃ በመነሳት ጎንደር በመግባት ሕወሃትን የተፋለሙበትን ቅጽበት አብራርተዋል።
ቀኑ በርካታ ወገኖች መስዋዕት የከፈሉበት ነው ያሉት ደግሞ የበዓሉ ታዳሚዎች ናቸው። ታዳሚዎቹ የማንነት ትግሉ ዳር እስኪደርስ ሁሉም በጋራ እንዲታገልም ጥሪ አቅርበዋል።
በበዓሉ ላይ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የሁመራ ከተማ የሥራ ኀላፊዎች፣ አርቲስቶች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።
#ሁመራ:ሐምሌ 05/2018 ዓ.ም
ዘጋቢ፦አምሳሉ አሞኘ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
