📣 የጠራ እና ግልጽ የመረጃ ፍሰት ሀገርን በምክክር ለማሻገር የሚኖረው ወሳኝነት 🕊️

31

 

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በተለየ በምክክር ችግሮቿን አስወግዳ በአንድነት ወደፊት መጓዝን አስቀድማለች።

እነ ደቡብ አፍሪካ፣ ቱኒዚያ እና ሌሎችም የዓለም ሀገራት ለሀገራዊ ምክክር ትኩረት በመስጠት ከግጭት አዙሪት ወጥተው የሰላም አየር ተንፍሰዋል። ኢትዮጵያም ለረጅም ዘመናት የተከማቹ ሕዝብ እና ሀገርን እረፍት የነሱ ችግሮችን ለመፍታት በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ጠረጴዛ መነጋገርን መርጣለች።

11 አባላት ያሉትን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በማቋቋም ላለፉት አራት ዓመታት የአጀንዳ እና የተሳታፊ ልየታን ጨምሮ ወሳኝ ሂደቶችን ሲያከናውን ቆይቷል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ 4 ሺህ የኢትዮጵያ ወኪሎች በተገኙበት ዋናውን ምክክር ለማካሄድ እየተንደረደረች ነው።

“ሪሰርች ጌት” ምሁራን የጥናት ውጤቶቻቸውን የሚያጋሩበት ዓለም አቀፍ የማኅበራዊ ትስስር ድረ -ገጽ ነው። በዚህ ገጽ ላይ “የሀገራዊ ምክክሮች ስኬት እና ውድቀት – የተመረጡ ሀገራት የጉዳይ ጥናቶች እና ለኢትዮጵያ የሚኾኑ አጠቃላይ ትምህርቶች” በሚል የተጋራው የጥናት ውጤት ከ2010 ዓ.ም በፊት የዚህን አጀንዳ ወሳኝነት ዝቅ አድርገው ተመልክተውት እንደነበር ይገልጻል። ውይይቱን ለማድረግ ትክክለኛው ጊዜ ላይ አልደረስንም የሚል መከራከሪያም ያነሱ እንደነበር አስታውሷል።

ጥናቱ ሀገራዊ ምክክር ግን ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ፋይዳ እጅግ የጎላ ነው ይላል። በተለይም በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ልዩ ልዩ የፖለቲካ ጎራዎች እና ማኅበረሰቦች የሻከረ ግንኙነታቸውን እንዲያድሱ ትልቅ ሚና ይጫወታል ይላል ጥናቱ። አወዛጋቢ በኾኑ አጀንዳዎች ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ምቹ መደላድል መኾኑንም አስምሮበታል።

በዚህ ሂደትም በተለያዩ አካላት መካከል የተፈጠረውን መራራቅ በማስወገድ የአብሮነት እና የትብብር መንፈስን ለማጠናከር ያግዛልም ብሏል።

የምክክር ሂደቱ ስኬታማ እንዲኾን ግን የሁሉም ባለድርሻ አካላት አሳታፊነት ትልቁን ስፍራ እንደሚወስድ ጥናቱ አትኩሮት ሰጥቷል። በመንግሥት፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች እና በሲቪክ ማኅበረሰቡ ዘንድ የሀገራዊ ባለቤትነት ስሜት ሊኖር ይገባል፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም በሂደቱ ያለፉ ሀገራትን ስኬት እና ውድቀት መሠረት በማድረግ ለስኬታማነቱ ሁሉንም ያሳተፈ እንዲኾን በልዩነት ሠርቷል።

ጠንካራ የፖለቲካ ፍላጎት እና ሰፊ የሕዝብ ድጋፍም ለሂደቱ ወሳኝነት በጉልህ ይነሳል። የሕዝብ ድጋፍ መኖር ወይም አለመኖር የውይይቱን ሂደት በእጅጉ ይወስነዋል። ኅብረተሰቡ ድጋፍ እንዲሰጥ ደግሞ በቂ መረጃ ሊኖረው ይገባል። መረጃ የሌለው ሕዝብ ሀሳብ ማካፈልም ኾነ የውይይቱን ውጤት ተቀብሎ መደገፍ ይከብደዋል። ስለኾነም የውይይቱ ሕጋዊነት እና የሕዝብ ተሳትፎ በሚዲያ እና በመረጃ ፍሰት ላይ የተመሠረተ ነው።

ጥናቱ ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ይህንን መማር እንደሚገባ ያብራራል። በኢራቅ ብሔራዊ ውይይት ወቅት የሚዲያ ሽፋን ዝቅተኛ እንደነበር ጠቁሟል። የውይይቱ ፕሮግራምም የተወሰነው በድንገት መኾኑን ጠቁሟል። ይህ የመረጃ እጥረት ሂደቱን ጥቂት የፖለቲካ ልሂቃን ብቻ እንዲቆጣጠሩት አድርጓል ነው የሚለው ጥናቱ።

በሱዳን ደግሞ ውይይቱ በአንድ አዳራሽ ውስጥ ብቻ የተወሰነ እንደነበር ጥናቱ ያስታውሳል። መንግሥት በወሰደው አፋኝ እርምጃም የተቃዋሚዎች ተሳትፎ አነስተኛ እንዲኾን አድርጓል።
በቱኒዚያም በተመሳሳይ ሂደቱ በፖለቲካ ልሂቃን በመመራቱ የሕዝብ ተሳትፎ ደካማ ነበር። እነዚህ ሁሉ ክፍተቶች የውይይቶቹን ተአማኒነት እና አፈጻጸም ክፉኛ እንደጎዱት ይገልጻል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ሂደት ከበርካታ ሀገራት ተሞክሮዎችን እንደመውሰዱ መጠን የመረጃ ፍሰትን እና የሥራ ግልጽነትን ታሳቢ አድርጎ ሢሠራ ቆይቷል። የሕዝብ ተደራሽነትን የሚያሰፉ ሥራዎችም በስፋት ሠርቷል። ሚዲያዎችም የእያንዳንዱን ሂደት እርምጃዎች በጥንቃቄ በመከታተል ሲዘግቡ ቆይተዋል።

ታዲያ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ስኬታማ እንዲኾን እና የሁላችንም ባለቤትነት እንዲረጋገጥ እንደ ዜጋ ትክክለኛ መረጃን በማግኘት እና በማጋራት በኩል የእርስዎ ሚና ምን ሊኾን ይገባል ይላሉ?

ሚዲያዎቻችንስ በቀጣይ ከዚህ የተሻለ ምን ሊሠሩ ይችላሉ? ሀሳብዎን ያካፍሉን!

#ሀገራዊምክክር #ኢትዮጵያ #የመረጃፍሰት #ሰላምናአንድነት #የዜጎችተሳትፎ #NationalDialogue #Ethiopia #MediaRole
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ4_2018_ዓ_ም

በስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየፌዴራል ፖሊስ ለሜቄዶኒያ ማዕከል የ2 ሚሊዮን ብር እና የአምቡላንስ ድጋፍ አደረገ።
Next articleበሁመራ እና አካባቢው የተመዘገቡ የልማት እና የሰላም ስኬቶች !