“ዛሬ በጎ ልብ በማሳየት ያገዝናቸው ታዳጊዎች በቀጣይ የማኅበረሰቡ አጋዥ ናቸው” ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥዬ

7
​የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) የነገዋን ሀገር የምንረከብበትን ብቁ ትውልድ ለመቅረጽ በሚደረገው ዘርፈ ብዙ ጥረት ውስጥ የበኩሉን አሻራ እያኖረ ይገኛል። ተቋሙ በትምህርት ዘርፉ ቁሳቁስ ማሟላት ለማይችሉ እና በተለያዩ ምክንያቶች ለተቸገሩ ተማሪዎች እገዛ የሚውል የትምህርት ቁሳቁስ ከተቋሙ የሥራ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች የማሠባሠብ መርሐግብር በይፋ አስጀምሯል።
​ይህ ንቅናቄ ሚዲያ መረጃ ማድረሻ ብቻ ሳይሆን፣ በተግባር ማኅበረሰብን መገንቢያና የትውልድ ቀራጭ ትልቅ ተቋም መኾኑን በተግባር ያሳየ ነው።
💡የጋራ ጥረት ለተተኪ ትውልድ፦ በመርኃ ግብሩ የተገኙት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ ባስተላለፉት መልእክት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠሩ ሕይወታቸውን እየደጎሙ ለሚማሩ እና የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላት ለማይችሉ ተማሪዎች የሚበረከተው ትንሽ ስጦታ ለእነሱ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑን አስገንዝበዋል።
“እኛ በወላጆቻችን እና በአጋዦቻችን እገዛ ተምረን እዚህ ተገናኝተናል፤ ባንማር ኑሮ አብረን እየሠራን ያለን ሰዎች አንገናኝም ነበር” ያሉት ዋና ሥራ አሥፈጻሚው፣ ታዳጊ ወንድም እህቶችን በማገዝ ተተኪ ማፍራት የዜግነት ግዴታ መኾኑን ገልጸዋል። ዓላማውን ለማሳካት የአሚኮ ቤተሰቦችም መረባረብ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
💡የህሊና እርካታና ምሁራንን የማፍራት ጉዞ፦ ብቁ፣ አስተዋይ እና ተመራማሪ ትውልድ ለማፍራት እገዛ የሚፈልጉ ተማሪዎችን በትምህርት ቁሳቁስ መደገፍ አስፈላጊ መሆኑን ጋዜጠኛ ሽመልስ ከበደ ተናግሯል።
💡“አንድ ደብተር ለልጄ” ከፍ ብሎ ቀጥሏል፦ ጋዜጠኛ ፍሬሕይወት ይልቃል በበኩሏ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከመደበኛ ተግባሩ ባሻገር ብዙ ማኅበረሰባዊ አገልግሎቶችን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሳለች። “አንድ ደብተር ለልጄ” የተሰኘው ንቅናቄ ባለፈው ዓመት በተቋሙ ተጀምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የትምህርት ቁሳቁስ ለክልሉ ትምህርት ቢሮ መረከቡን አስታውሳለች። ዘንድሮ ደግሞ እያንዳንዱ ሠራተኛ ይለግስ የነበረውን አምስት ደብተር ወደ አንድ ደርዘን ከፍ ማለቱን ገልጻለች።
ዛሬ በጎ ልብ በማሳየት የታገዙ ተማሪዎች በቀጣይ በልዩ ልዩ ዘርፎች መልሰው ማኅበረሰቡን ያግዛሉ። ሰው ለህሊናው እርካታ እና ለመንፈሳዊ በረከት ሲል ድጋፍ ለሚፈልጉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከትምህርት ቁሳቁስ ባሻገር የቻለውን ድጋፍ ማድረግ ትውልድ ላይ ኀላፊነትን መወጣት ነው። እርሰዎ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ሀሳብ አለዎት? በአስተያየት መስጫ ሀሳበዎን ያጋሩን።
#ባሕር ዳር ሐምሌ 02 ቀን 2018 ዓ.ም
✍️ ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
Previous articleለጥንቃቄ፦ ሰርጎ ገብ ጥቃት አሳሳቢ ኾኗል።
Next articleበአማራ ክልል በቀጣይ ቀናት የሚጠበቀውን የአየር ኹኔታ ምን ይመስላል?