የደብረ ማርቆስ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ያገኘው ዓለም አቀፍ ዕውቅና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወዳደሩ ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያስችል ነው።

4
🎓
​የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በቴክኒክ እና ሙያ ዘርፍ የሥልጠና ጥራትን ለማረጋገጥ እየሠራ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ባደረገው ኦዲት መሠረት ዕውቅና ካገኙ የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች መካካል ደብረ ማርቆስ ፓሊ ቴክኒክ ኮሌጁ አንዱ ነው።
የደብረ ማርቆስ ፓሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አስጨነቅ ካሳ ኮሌጁ ላለፈው አንድ ዓመት ሲያከናውን የነበረውን ጥልቅ የውስጥ ዝግጅት እና የጥራት ማረጋገጫ ኦዲት በተሳካ ሁኔታ በማጠናቀቅ፣ የአይ ኤስ ኦ 21001:2018 የትምህርት ተቋማት አሥተዳደር ሥርዓቶች የተሰኘ ዓለም አቀፍ ዕውቅና አግኝቷል ብለዋል።
ይህ ስኬት ኮሌጁ የትምህርት አሰጣጥ ሂደቱን፣ የማሽን እና የቴክኖሎጂ አቅሙን፣ የሰነድ አያያዝ ሥርዓቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሳደግ የተደረገ ጥረት ውጤት መኾኑን ነው የተናገሩት። በተደረገው ኦዲትም ተቋሙ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጡ መስፈርቶችን በማሟላቱ ዕውቅናውን አገኝቷል ነው ያሉት።
​ይህ ዕውቅና ለተቋሙ፣ ለሠልጣኞች እና ለአካባቢው ማኅበረሰብ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።
ዕውቅናው ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች መካከልም
✅ በብቃት የታነጹ እና ለገበያ ዝግጁ የኾኑ ባለሙያዎችን ለኢዱስትሪዎች ለማቅረብ ዕድል ይፈጥራል።
✅ ለአካባቢው ማኅበረሰብም ብቁ የሰው ኀይል እና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማግኘት ለኢኮኖሚ ዕድገት የላቀ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
✅ተቋሙ ዓለም አቀፍ መኾኑ ከ2019 በጀት ዓመት ጀምሮ ተመራቂዎች የሚያገኙት የምስክር ወረቀት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ይኖረዋል። ይህም ተማሪዎች በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይኾን በዓለም አቀፍ የሥራ ገበያም ተወዳዳሪ እንዲኾኑ ያስችላቸዋል።
✅ የማሽኖች እና የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች በየጊዜው በኢንስቲትዩቱ ተፈትሸው አገልግሎት ስለሚሰጡ ተማሪዎች ወቅታዊ በኾኑ መሳሪያዎች በተግባር የታገዘ ክህሎት እንዲያዳብሩ ያደርጋል።
✅ዕውቅናው ለሦሥት ዓመት የሚቆይ ነው። በየዓመቱ የሚደረግ የክትትል ኦዲት ይኖራል። ተቋሙ ደረጃውን እንዲጠብቅም ያደርጋል።
✅ተማሪዎች ከመደበኛው ሥልጠና ባለፈ የፈጠራ ክህሎታቸውን የሚያዳብሩበት፣ የሚመዘኑበት እና የተሻለ ተጠቃሚ የሚኾኑበት ዕድልም ይፈጥራል።
✅የትምህርት አሰጣጥ ጥራቱን በማሳደግ ብቁ፣ ተወዳዳሪ እና ሥራ ፈጣሪ ዜጎችን ለማፍራት የበለጠ ለመሥራት የሚያግዝ ነው ብለዋል።
ይህ ስኬት በሀገር አቀፍ ደረጃ የቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠናን ጥራት ከፍ ለማድረግ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ይጠበቃል።
ዘጋቢ፦ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየመከሩ ሀገር አኖሩ
Next articleለጥንቃቄ፦ ሰርጎ ገብ ጥቃት አሳሳቢ ኾኗል።