የመከሩ ሀገር አኖሩ

3
ለኢትዮጵያውያን ሀገር መገንባት አዲስ ነገር አይደለም። የታሪክ መዛግብት ሲገለጡ የኢትዮጵያ ስም ከጥንታዊ ሥልጣኔዎች አንዱ ኾኖ ይነበባል።
ኢትዮጵያውያን የመንግሥት አሥተዳደር መሥርተን፣ ሕግና ሥርዐት አበጅተን፣ በሃይማኖት ታንጸን፣ በጀግንነት ሀገር ጠብቀን፣ በሥነጽሑፍ ተጠብበን፣ ማኅበራዊ ቁርኝታችንን አጥብቀን ለሺህ ዘመናት የኖርን የታላቅ ሀገር ዜጎች ነን ብሏል።
ታሪካችን ሲነበብ እልፍ አኩሪ ገድሎች ይዘረዘራሉ። የአፍሪካ የነፃነት ቀንዲልነታችን ብቻውን ማንነታችን ከድል፣ ከክብር እና ከእፁብ ድንቅ እሴቶች የተሸመነ መኾኑን ይመሰክራል።
በረዥሙ የሀገርነት ታሪካችን የተፈጠሩ የሀሳብ አለመግባባቶች ግን አንድ ቦታ ላይ ያልተጠገነ ስብራት ፈጥረውብናል። ይኸውም ልዩነቶችን በኃይል የመፍታት ልማድ ነው። ከጠመንጃ አፈሙዝ ሥልጣንን ለማመንጨት የተጓዝንባቸው መንገዶች ክፉኛ አቁስለውናል። ትርክቶች ሥር ሰድደው አጋጭተውናል። ሰላማዊ የፖለቲካ ውይይት ባለመዳበሩ እርስ በእርስ ለመሸናነፍ ተማምለን ማንንም ሳይኾን ራሳችንን ጎድተናል።
ሀገራዊ ምክክር ብቸኛው ዘላቂ የሰላም ጎዳና ስለመኾኑ በተለያዩ ጊዜያት በሀገር ወዳድ ዜጎች ምክረ ሀሳብ ቢቀርብም ሰሚ ጆሮ ሳያገኝ ያለመግባባት መንስኤዎች ተጠናክረው ቀጥለው ነበር።
እነኾ አሁን ኢትዮጵያ እየመከረች ነው። ልጆቿ ከአራቱም አቅጣጫ ተሰባስበው ለዘመናት የዘለቁ ያለመግባባት መንስኤዎችን ለማከም ቀን ቆርጠው እየጠበቁ ነው። ሀገር መገንባት፣ ትውልድ ማሻገር እና እሴት ማስቀጠል የሚያውቁት ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን በምክክር ለማጽናት ተዘጋጅተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ልጆች ሀገር የተሸረሸሩ መልካም እሴቶቿን የምታድሰው በምክክር መኾኑን በተግባር ሊያሳዩ በመዲናቸው እየተሰባሰቡ ነው፡፡
በመመካከር ኹላችንም እናሸንፋለን፡፡ በመመካከር መግባባትን እንፈጥራለን፡፡ በመመካከር ያልሻሩ ቁስሎችን እናክማለን፡፡ ይህን ጠንቅቀው የተገነዘቡት ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ዳግም በዓለም ፊት አብሪ ኮከብ ለማድረግ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤውን እየተጠባበቁ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ልጆች ዛሬም ሀገራቸው ባለመግባባት ሕመም መቸገሯን ሊያክሙ የመፍትሔ ሀሳባቸውን አዘጋጅተዋል፡፡
ግጭት ሀገርን ያፈርሳል፡፡ መቃቃርን ያባብሳል፡፡ ሰላምን እንዳትመለስ አድርጎ ያሸሻታል፡፡ ሀገር በዘላቂነት ሰላም የምትፈጥረው፣ ማኀበራዊ ቁርኝት የሚጠናከረውና ሀገራዊ መግባባት የሚፈጠረው በምክክር ብቻ ነው፡፡
በምክክር ሀገራዊ መግባባት እንፍጠር፤ ኢትዮጵያን ለትውልድ እናሻግር ብሏል የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባስተላለፈው መልዕክት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleዛሬ የምናደርጋት በጎ ተግባር ነገ ለምታብብ ውብ ዓለም መሠረት ናት።