
የሰው ልጅ ሕይወት ትርጉም የሚኖረው ለራስ ከመኖር አልፎ ለሌሎች መትረፍ ሲቻል ነው። በዚህ ምድር ላይ ካሉ ንጹሕ እና ክቡር ተግባራት መካከልም በጎ ፈቃድ አገልግሎት አንዱ ነው።
በጎ ፈቃደኝነት ያለምንም ቁሳዊ ወይም የገንዘብ ክፍያ ከልብ በመነጨ ፍላጎት እና ፍቅር የሌሎችን ሕይወት ለመቀየር እና ማኅበረሰብን ለመደገፍ የራስን ጊዜ፣ ዕውቀት እና ጉልበት በነጻ መስጠት ነው። ብዙዎቻችን ዓለምን ለመቀየር ትልልቅ ነገሮችን እናስባለን። ነገር ግን እውነተኛው ለውጥ የሚጀምረው ከቀላል የበጎ ፈቃድ ተግባር ነው።
በጎ ፈቃደኝነት የበጎ ሰዎች የልብ ጥሪ ነው። በጎ ልቦች አቅመ ደካሞችን በመርዳት፣ አካባቢን በማጽዳት እና አረንጓዴ በማድረግ፣ ወላጆቻቸውን ያጡ ሕጻናትን በመንከባከብ እና ዕውቀትን ለሌሎች በማካፈል ለዓለም ብርሃን የሚፈነጥቁ ሻማዎችን የሚፈጥሩ ናቸው።
የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዋ ያለምወርቅ አድማሱ በራሳቸው አቅም ቤታቸውን መጠገን ባለመቻላቸው ለመውጣት እና ለመግባት አስቸጋሪ በነበረች ቤት ውስጥ ለረጅም ጊዜ ይኖሩ ነበር። ባለፈው ዓመት የክረምት ወቅት ግን ቤታቸው በበጎ ፈቃድ አገልግሎት መጠገኑን ነግረውናል። ቤታቸው በመጠገኑ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
“ቤቴ ያጎነበሰች ነበረች ቀናብየ መግባት ችያለሁም’ ብለዋል። ዘንድሮም ሌሎች ሰዎች የእኔ ዓይነት ዕድል አግኝተው ቤታቸው ቢጠገንላቸው ደስ ይለኛል ነው ያሉን።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ በባሕር ዳር ከተማ በተደረገው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የማስጀመሪያ መርሐ ላይ እንደ ክልል 15 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ እንሚኾኑ መናገራቸው ይታወሳል።
በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 17 ዋና ዋና አገልግሎቶች ተካትተዋል። 9 ነጥብ 8 ሚሊዮን በጎ ፈቃደኞች ይሳተፋሉ ተብሎም እንደሚጠበቅ አንስተዋል፡፡ በክልሉ 100 የበጎ ፈቃድ ሞዴል ቀበሌዎችን ለመፍጠርም እየተሠራ መኾኑንም ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ወይዘሮ ያለምወርቅ ላሉ በክልሉ የሚገኙ ከ18 ሺህ በላይ አቅመ ደካሞችን እና ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ቤቶች ግንባታ እንደሚከናወንም ገልጸዋል። በአጠቃላይ 20 ቢሊዮን ብር የሚገመት አገልግሎት ይሰጣል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የ2018 ዓ.ም ክልላዊ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎትን ባስጀመሩበት ወቅት በጎነት የኢትዮጵያውያን የመረዳዳት፣ የመደጋገፍ ባሕል እና እሴት መገለጫ እንደኾነ ተናግረዋል።
በራስ ተነሳሽነት ሀገር እና ወገንን ለመረዳት ለበጎ ዓላማ በጋራ የመትጋትን ያህል መልካም ተግባር የለም ነው ያሉት። በጎ ፈቃደኝነት በቅንነት ላይ የተመሠረተ የመተሳሰብ ውጤት መኾኑንም ገለጸዋል።
በጎ ተግባር የሚቀይረው የሀገራችን ገጽታ እና የሚለውጠው የሕዝባችን ሕይወት ነው ብለዋል። ዛሬ የምናከናውነው በጎ ተግባር ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገት ጉልህ ሚና ይጫወታል፣ የልማት ሥራዎችንም ያቀላጥፋል ነው ያሉት። በዋጋ የማይታመን የመንፈስ እርካታንም ያጎናጽፋል ብለዋል። በጎ ፈቃደኝነት በወቅት የሚገደብ ብቻ ሳይኾን የማኅበረሰቡ የዘወትር ተግባር እና ባሕል ኾኖ መቀጠል እንደሚኖርበትም አመላክተዋል።
በጎ ፍቃደኛ ስንኾን ውስጣዊ ሰላም እና ደስታን እናገኛለን። ሌላውን ሰው መርዳት በራስ ውስጥ የሚፈጥረው እርካታ በገንዘብ ሊገዛ የማይችል ታላቅ ሀብት ነውና። በጎ ፍቃደኛ ስንኾን አዳዲስ ክህሎቶችን እናዳብራለን። በጎ ፍቃደኛ ስንኾን ታላቅ ማኅበራዊ ትስስር እንፈጥራለን።
በጎ ፈቃደኝነት የጥቂት ሀብታሞች ወይም ትርፍ ጊዜ ያላቸው ሰዎች (ተቋማት) ሥራ አይደለም። ፍቅር፣ ርህራሄ እና ቅንነት ያላቸው የሁሉም የዋህ ልቦች ጥሪ ነው። ዛሬ የምናደርጋት አንዲት በጎ ተግባር ነገ ለምታብብ ውብ ዓለም መሠረት ናት።
እጅዎን ለበጎ ፈቃድ ይዘርጉ፤
የሰው ልጅ እና ዓለም የእርስዎን ደግነት ይፈልጋሉና!
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
