
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና ቦይንግ ኩባንያ ጋር በትብብር መሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል። የዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት በኤሮስፔስ ምህንድስና በአቪየሽን ዘርፍ ከቦይንግ ጋር በትብብር ለመሥራት ነው ስምምነት ነው የተፈራረሙት።
የቦይንግ ኩባንያ የአፍሪካ ማኔጅንግ ዳይሬክተር አምባሳደር ሔኖክ ተፈራ በመግባቢያ ስምምነቱ ላይ ቦይንግ የዓለማችን ግዙፉ የአቪየሽን እና የኤሮስፔስ ኩባንያ ነው ብለዋል። ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በኢትዮጵያ ግዙፉ የአቪየሽን ምሕንድስና ትምህርት የሚሰጥ ተቋም በመኾኑ አጋርነቱ ቀደም ብሎ መኾን የነበረበት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአቪየሽን ዘርፍ የያዘችውን ትልቅ ራዕይ እንዲሳካ የሰው ኃይል ላይ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። ለዚህም እንደ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ያሉ ተቋማት በአቪየሽን ዘርፍ ባለሙያዎችን ለማሠልጠን የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ወሳኝ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።
በስምምነቱ መሰረት ቦይንግ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢኖቬሽን ማዕከል ተጠናክሮ እንዲመሠረት ያለውን አቅም እና ዕውቀት ያበረክታል ብለዋል። በአቪየሽን እና ኢኖቬሽን ማዕከሉ አስተማሪዎችን በማሠልጠን እና ለተማሪዎች የተግባር ልምምድ ዕድል በመስጠት በጋራ እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያም በአቪየሽን እና ኤሮስፔስ ማኑፋክቸሪንግ ያላትን ጥሩ ጅምር አጠናክሮ ለማስቀጠል ከሀገሪቱ ተቋማት ጋር ይሠራል ነው ያሉት።
በሚቀጥሉት 20 ዓመታት የአፍሪካ አቪየሽን ኢንዱስትሪ አዲስ 74 ሺህ ባለሙያዎችን ይፈልጋል ያሉት ዳይሬክተሩ ፍላጎቱን ለማሟላት ኢትዮጵያ ወሳኝ ሚና ትጫወታለች ብለዋል።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት መንገሻ አየነ (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው በቴክንሎጅ ዘርፍ ሰፋ ያለ ሥራ እየሠራ ነው ብለዋል። የሚሰጡ የምሕንድስና መርሐ ግብሮች በዓለም አቀፍ እውቅና ሰጪ ተቋማት እውቅና እንዲያገኙ በማድረግ የዘርፉ ተማሪዎች በዓለም አቀፍ ገበያው ተሳታፊ እያደረገ የሚገኝ በኢትዮጵያ ቀዳሚው ዩኒቨርሲቲ መኾኑን አመላክተዋል።
ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር የመርከበኛ ሥልጠና ማዕከል በማቋቋም በማሪታይም አካዳሚ ባለፉት አሥር ዓመታት ከ3 ሺህ በላይ የባሕር ላይ መርከበኞች ማሠልጠኑን ነው የጠቀሱት።
በሌላ በኩል ባለፉት አራት ዓመታት ካሪክለም ተቀርጾ በኤሮስፔስ ምሕንድስና ልዩ ክሕሎት ያላቸውን ተማሪዎች ወደ ዘርፉ በማስገባት የማስተማር ሥራ መጀመሩን አንስተዋል። ዘርፉ ካለው ስፋት እና ጥልቀት፤ ከሚያስፈልገው የተግባር ልምምድ አኳያ የመማር ማስተማሩን ለማስቀጠል ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በትብብር እየሠሩ መኾኑን ገልጸዋል። ዋነኛ አጋራችን ደግሞ ቦይንግ ነው ብለዋል።
ወደፊት ከቦይንግ ጋር በመተባበር ዘርፉን በላቀ ደረጃ በማገዝ፣ ሥርዓተ ትምህርቱን በማሻሻል፤ በዘርፉ ሠልጥነው የሚወጡ የዩኒቨርሲቲውን ተማሪዎች በተለይም ቦይንግ ባለበት ዓለም ሁሉ ተወዳዳሪ ኾነው እንዲወጡ ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት። ይህን ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው ቁርጠኛ መኾኑን ገልጸዋል።
የኤሮስፔስ ምሕንድስና በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ታጥሮ የሚቆይ ሳይኾን እንዱስትሪው ጋር በቅርበት መተሳሰር እና የላቀ የመማር ማስተማር ሂደት የሚፈልግ በመኾኑ ከቦይንግ ጋር የተፈጸመው የመግባቢያ ሥምምነት ዋነኛ መግቢያ በር ይኾናል ነው ያሉት። በተለይ ለተማሪዎች ትልቅ በር ተከፍቷል ያሉት ፕሬዝዳንቱ በተከፈተው በር አልፎ ራስን እና ሀገርን መጥቀም ይጠበቃል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው ኢትዮጵያ የጀመረችውን ተልዕኮ ለማሳካት ከኤሮስፔስ በተጨማሪ በኒውክሌር ምሕንድስና፣ በሳይበር ደኅንነት እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘርፍም ፕሮግራሞችን የመቅረጽ እና የመማር ማስተማር ሥራን እያከናወነ መኾኑን አመላክተዋል።
በአድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
