
ባሕር ዳር: ሐምሌ 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ወቅቱ አርሶ አደሩ ዘር የሚዘራበት ነው። ለዚህ ሥራ ደግሞ ዝናብ ማግኘት ወሳኙ ነገር ነው። ለመኾኑ በአማራ ክልል በቀጣይ ቀናት የሚጠበቀው የአየር ኹኔታ ምን ይመስላል?
በምዕራብ አማራ የሚቲዮሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል የሚቲዮሮሎጂ ሳይንስ ረዳት ተመራማሪ እንደግ አንለይን ጠይቀናል።
ተመራማሪው እንዳሉት ባለፉት አስር ቀናት በምዕራብ አማራ በአብዛኛው ዞኖች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ተመዝግቧል።
በአዊ ዞን እና አካባቢው ደግሞ እስከ 30 ሚሊ ሜትር እና ከዚያ በላይ የሚደርስ ከባድ ዝናብ መመዝገቡን ገልጸዋል።
በአንጻራዊነት በምሥራቅ አማራ ደረቅ የአየር ኹኔታ የተመዘገበበት ነበር። ነገር ግን ከሰኔ 30 ጀምሮ በሰሜን ሸዋ፣ ኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን፣ ደቡብ ወሎ እና በጥቂት ሰሜን ወሎ አካባቢዎች ቀላል መጠን ያለው ዝናብ ተመዝግቧል ነው ያሉት።
በቀጣይ አስር ቀናት የዝናብ መጠኑም ይኹን የሥርጭቱ ኹኔታ እየተሻሻለ እንደሚሄድ ይጠበቃል አሉ ተመራማሪው።
በምዕራብ አማራም ኾነ በምሥራቅ አማራ ዞኖች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ይጠበቃል ነው ያሉት።
በተለይም በምዕራብ አማራ (አዊ ዞን፣ ምሥራቅ እና ምዕራብ ጎጃም፣ እንዲኹም ማዕከላዊ ጎንደር) ደግሞ ከ30 ሚሊ ሜትር በላይ የኾነ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ኹኔታዎች ይጠቁማሉ ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
