የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው እና የኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ !

4
📈
ኢትዮጵያ ከሐምሌ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ገብታለች። ማሻሻያው የመንግሥትን ገቢ ማሳደግ እና የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት በገበያ ሥርዓት እንዲወሰን ማድረግን ዓላማ ያደረገ ነው።
በመደበኛው እና በጥቁር ገበያው መካከል ያለውን የውጭ ምንዛሬ ልዩነት ማጥበብም ዋነኛ ግቡ ነው።
በአጠቃላይ ማሻሻያው የኢኮኖሚ መዛባትን ማረቅ እና የንግድ አሠራርን ማዘመን እንደኾነም ይነገራል።
ምቹ ያልኾነ የውጭ ምንዛሬ አሠራር አልሚዎችን የሚፈታተን ማነቆ ኾኖ መቆየቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ የነበሩት ማሞ ምህረቱ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ወደ ማክሮ ኢኮኖሚ መግባቷን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር ገልጸው ነበር።
አሁን ተግባራዊ የተደረገው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ይህንን እንቅፋት በማስወገድ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር ዕድል እንደሚሰጥም ተናግረዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በቅርቡ በነበረ መድረክ እንዳብራሩት መንግሥት የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በመተግበር ሀገሪቱ ገጥሟት የነበረውን ከፍተኛ የዋጋ ንረት፣ የዕዳ ጫና እና የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ቀውስ መቅረፍ ችሏል።
በዚህም ባለፉት ሰባት ዓመታት የመንግሥት አጠቃላይ ገቢ በአምስት እጥፍ ያደገ ሲኾን የታክስ፣ ታክስ ያልኾኑ ገቢዎች እና የውጭ ሀብት ፍሰቶች በከፍተኛ ሁኔታ ጨምረዋል ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በ6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ የኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢትዮጵያን ዕድገት በጉልህ እያንጸባረቀ መኾኑን በቁጥራዊ አኃዞች አስደግፈው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት እስከ 10 ነጥብ 3 በመቶ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።
በወጪ ንግድ በኩል ሀገሪቱ ታሪካዊ ስኬት አስመዝግባለች ነው ያሉት። የዘንድሮው ኤክስፖርት ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ ኾኗል ብለዋል።
ይህም ሀገሪቱ ባለፉት 17 ዓመታት በድምሩ ከላከችው ጋር እኩል እንደኾነም ገልጸዋል።
ከቡና ኤክስፖርት 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል። ይህም ኢትዮጵያን በዓለም ከብራዚል እና ኮሎምቢያ ቀጥሎ 3ኛዋ ትልቅ ቡና ላኪ አድርጓታል ነው ያሉት።
ከወርቅ ዘርፍ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ 5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል። ይህም ባለፉት 27 ዓመታት ከተገኘው 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ጋር ሲነጻጸር እጅግ ከፍተኛ ኾኖ የተመዘገበ ነው ብለዋል።
38 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ካፒታል ወደ ሀገር ውስጥ ፈሰስ መደረጉም የማሻሻያው ሌላኛው ማሳያ ነው። የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ክምችትም በ20 እጥፍ ማደጉን ጠቁመዋል።
የሀገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብም በከፍተኛ ሁኔታ ተሻሽሏል። በለውጡ መጀመሪያ 170 ቢሊዮን ብር የነበረው ገቢ አሁን ከ1 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ብር በላይ መድረስ ችሏል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ይህ የተሳካው በዲጂታላይዜሽን እና 43 ሺህ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎችን ወደ ሕጋዊ መስመር በማስገባት ነው ብለዋል።
የገንዘብ ሚኒስቴር ከብሔራዊ ባንክ መበደር አቁሟል። በምትኩ የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭን በመጠቀም የበጀት ጉድለቱን በጤናማ መንገድ መሸፈን መቻሉም የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ አወንታዊ አስተዋጽኦ ማሳያ ኾኖ ተነስቷል።
በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
#ምስል ከአርካይቭ
Previous articleከሽፋን ወደ ጥራት፤ የኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ አዲስ ጉዞ !
Next articleከዕርዳታ ጥገኝነት ወደ ዘላቂ ምርታማነት።