ከዕርዳታ ጥገኝነት ወደ ዘላቂ ምርታማነት።

4
​በአማራ ክልል በየዓመቱ በታላቅ ሕዝባዊ ንቅናቄ የሚከናወነው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘንድሮ “በጎነት ለሀገር ሉዓላዊነትና ለሕዝብ ተጠቃሚነት” በሚል መሪ መልእክት በላቀ የተቀናጀ ዝግጅትና በልዩ ቁርጠኝነት ወደ ተግባር መገባቱን የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ አባይ መንግስቴ አስታውቀዋል።
​ኃላፊው እንደተናገሩት፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ቀደም ሲል ከነበረው የወቅታዊና የአጭር ጊዜ ዕርዳታ አቅርቦት ልማዳዊ አሠራር በመውጣት፣ ዜጎች ራሳቸውን ችለው ወደ ምርታማነት እንዲሸጋገሩ የሚያስችል የዘላቂ ኑሮ ማሻሻያ ዕቅድን አንግቦ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
📌 የዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ዋና ዋና ምሰሶዎች፦
🏠 ለአቅመ-ደካሞች ዘላቂ የገቢ ምንጭ፡ የአረጋውያንና አቅመ-ደካሞችን መኖሪያ ቤት ከመጠገን ባሻገር፤ በዘላቂነት ራሳቸውን መመገብና ቋሚ ገቢ ማግኘት የሚችሉባቸው የዶሮ እርባታ፣ የጓሮ አትክልት ልማትና የከብት ማድለብ ሥራዎች እንዲመቻቹላቸው እየተደረገ መሆኑን አቶ አባይ ጠቁመዋል።
🥑 የአረንጓዴ አሻራ ከምግብ ዋስትና ጋር፡ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ ከምግብ ዋስትና እና ከኢኮኖሚ ጥቅም ጋር ቀጥተኛ ትስስር እንዲኖረው መደረጉን የገለጹት ኃላፊው፤ ለዚህም ከፍተኛ የገበያ ዋጋ ያላቸው እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ቡና እና ሌሎች የፍራፍሬ ችግኞች ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ በስፋት እየተተከሉ መሆኑን አስታውቀዋል።
💼 ለወጣቶች ምቹ የሽግግር ሥርዓት፡ በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ላይ የሚሳተፉ የዩኒቨርሲቲ፣ የኮሌጅና የቴክኒክና ሙያ ምሩቃንን መንግሥት በማኅበራት በማደራጀት፣ የመነሻ ካፒታልና የመሥሪያ ቦታዎችን በማመቻቸት ወደ ቋሚ የኢንተርፕራይዝ ባለቤትነት የሚሸጋገሩበት ሥርዓት መዘርጋቱንም አቶ አባይ በሃሳባቸው አንስተዋል።
📚 የቤተሰብን የኢኮኖሚ ጫና መቀነስ፡ ለተማሪዎች የሚሰጠው ነፃ የማጠናከሪያ ትምህርት ወላጆች ያወጡት የነበረውን ከፍተኛ ወጪ ማስቀረቱንና በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት የሚቸገሩ ህጻናትን ዩኒፎርም፣ ደብተርና እስክርቢቶ በማሟላት ትውልድን ያለመዛነፍ የማስቀጠል ሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
🤝 ማኅበራዊ አንድነትና የታሪክ አሻራ ጥሪ!
​በዘንድሮው መርሃ ግብር የክልሉ ወጣቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የጸጥታ አካላት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ሀገር በቀል ድርጅቶችና ባለሀብቶች በላቀ ተነሳሽነት እየተሳተፉበት ይገኛል።
​ይህ ማኅበራዊ መስተጋብር መንግሥት በጅቶ ለመፈፀም የሚያዳግተውን በቢሊዮን የሚቆጠር በጀት በመጋራት፣ ቀሪ አቅም ወደ ሌሎች መሠረታዊ የልማት ዘርፎች እንዲዞር ትልቅ ዕድል መፍጠሩን አቶ አባይ መንግስቴ አስገንዝበዋል።
​”የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ወቅታዊ ተግባር ብቻ ሳይሆን የክልላችንን ልማትና የብልጽግና ጉዞ የሚያፋጥን ስትራቴጂካዊ የልማት መሣሪያ ነው” ያሉት ኃላፊው፤ እያንዳንዱ ዜጋ የታሪክ አሻራውን ያኖር ዘንድ መላው የክልሉ ማኅበረሰብና የልማት አጋሮች የጀመሩትን ድጋፍና አጋርነት አጠናክረው እንዲቀጥሉ የክልሉ መንግሥት ጥሪ ማስተላለፉን ገልጸዋል።
#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 01/2018 ዓ.ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው እና የኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ !