3

 

6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ሥብሠባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት በማካሄድ ላይ ይገኛል።

ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎችም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ምላሽ እና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ የተካሄደውን ሀገራዊ ምርጫ በተመለከተ ሲያብራሩ ሂደቱ የኢትዮጵያን ሕዝብ የረጅም ዘመናት የማኅበራዊ ካፒታል ባለጸጋነት እና በቀላሉ ሊገመት የማይችል ሕዝብ መኾኑን በተግባር ያረጋገጠ ነው ብለዋል።

በቀደሙት ዓመታት የሚፎካከሩ የፖለቲካ ኀይሎች እርስ በእርስ በሀሳብ ወይም በጉልበት ይወቃቀሱ የነበረ ቢኾንም በዚህኛው ምርጫ ግን ራሱ ምርጫው እንዳይካሄድ የጥቃት ኢላማ ተደርጎ እንደነበር አስታውሰዋል። ይሁን እንጂ ሕዝቡ “አትመዝገቡ፣ አትደግፉ፣ አትምረጡ” የሚሉ የተለያዩ የጥፋት ቅስቀሳዎችን፣ እገዳዎችን እና ማወናበጃዎችን ወደ ጎን በመተው በነቂስ ወጥቶ ድምጹን መስጠቱን ተናግረዋል።

በዚህ ታሪካዊ የምርጫ ሂደት ሕዝቡ ጽንፈኝነትን፣ ባንዳነትን እና ዘረኝነትን እንደማይፈልግ በአንድ ድምጽ ማረጋገጡን እና ዋነኛ ፍላጎቱም ተባብሮ የጋራ ሀገርን ማጽናት እና ማበልጸግ መኾኑን በተግባር አሳይቷል ነው ያሉት።

አረጋውያን ለቀጣይ አምስት ዓመታት ለልጆቻቸው ሀገር ሲሉ እንዲሁም ሕመምተኞች፣ በሀዘን ላይ ያሉ ወገኖች እና እናቶች ልጆቻቸውን አዝለው ወጥተው መምረጣቸው መንግሥት በትልቅ አደራነት የሚወስደው መኾኑን ጠቁመዋል።

ይህም ሕዝቡ ያለውን ጥልቅ አሳቢነት እና የሰላም ፈላጊነት ፍላጎት በግልጽ ያሳየ ስለመኾኑ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን ድምጽ የሰጠው መንግሥት ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚዎችን ለማሻሻል የሚያደርገውን ጥረት እና ጅምር በማድነቅ፣ ሥርዓታዊ ሌብነት መጥፋቱን በመደገፍ መኾኑን ገልጸዋል።

ኾኖም ይህ ድምጽ አሁንም በውስጥ ያሉ ሌቦችን በተቻለ መጠን አጥርቶ በማውጣት የአገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ ማሻሻል እና የሕዝብን ፍላጎት ማሳካት እንደሚገባ የተጣለ አደራ መኾኑን ተናግረዋል።

የጸናች እና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እና አሻራ ማሳረፍ እንዳለበትም አሳስበዋል።

#አሚኮ_ዜና #የምክር_ቤት_ውሎ #PMAbiyAhmed #Parliament

በስማቸው አጥናፍ

#ባሕር_ዳር_ሰኔ_30_2018_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር መንግሥት ምን እየሠራ ነው ?
Next article“የመንግሥት ምኞት የአባላቱ ተሳትፎ የመጨረሻ እንዳይኾን ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)