
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ሥብሠባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት በማካሄድ ላይ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከምክር ቤት አባላት ለተነሱት ጥያቄዎችም ምላሽ እና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በማብራሪያቸው እንደገለጹት ሰላም እንዲመጣ በርካታ ውይይቶች ሲካሄዱ ቆይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ዓመታት በ225 መድረኮች ከሃይማኖት አባቶች፣ ከመንግሥት ሠራተኞች፣ ከሀኪሞች፣ ከመምህራን እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በየደረጃው በብልጽግና ፓርቲ አማካኝነት ደግሞ ከ4ሺህ በላይ መድረኮች ተካሂደዋል ነው ያሉት። በሀገራዊ ምክክሩ ሂደትም በ100 ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች አጀንዳ የሚሰጡበት መድረኮች ስለመካሄዳቸውም አንስተዋል። እነዚህ ውጤቶች ግጭት እንዲቀንስ አድርገዋልም ብለዋል።
አሁንም ድረስ እያጋጠሙ ያሉ ግጭቶች ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ የሚፈልጉ የውጭ ኀይሎች ከውስጥ ባንዳዎች ጋር በቅንጅት የሚፈጥሩት ስለመኾኑም አንስተዋል።
ለዚህ መፍትሄው ሕዝብን በስፋት ማወያየት እና የጸጥታ ተቋማትን ማጠናከር መኾኑንም ተናግረዋል። ለዚህም የጸጥታ ተቋማት በቁጥር፣ በብቃት እና በቴክኖሎጂ እያደጉ መጥተዋል ነው ያሉት። ይህም ውጤት ማምጣቱን ገልጸዋል።
በየክልሎች የታጠቁ ኀይሎች ወደ ሰላም እንዲመጡ በተደጋጋሚ ጥሪ እንደተደረገላቸውም ተናግረዋል። በዚህም በርካቶች ጥሪውን ተቀብለው ወደ ሰላም መመለሳቸውን ጠቁመዋል።
በቀጣይም በመቀራረብ እና በመወያየት ግጭት ለማስወገድ እና ሰላምን ለማስፈን ጥረት ይደረጋል ነው ያሉት። የቀሩት ታጣቂዎችም እንዲመጡ እየተደረገ ያለው ጥረት እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
#አሚኮ_ዜና #የምክር_ቤት_ውሎ #PMAbiyAhmed #Parliament
በአሰፋ ልጥገበው
#ባሕር_ዳር_ሰኔ_30_2018_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
