🔥 መከላከያ ሠራዊት ዛሬም እንደትናንቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የማጽናት አቋም ላይ ነው”🔥 🇪🇹

103

 

ሥርዓቶች ሲለወጡ እርሱ ግን እንደ ዓለት ጸንቷል፤ አባላቱ ለሀገራቸው ሲሉ ያለስስት አካላቸውን አጉድለዋል፤ ሕይዎታቸውን ሰጥተዋል፤ ደማቸውን አፍሰው አጥንታቸውን ከስክሰዋል የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት። ⚔️💪

ስለ ሀገራቸው ሉዓላዊነት በየተራራ ሸንተረሩ ድንጋይ ተንተርሰው፤ ጤዛ ልሰው ተዋድቀል፤ ☀️ሀሩሩን ታግሰው 🌧️ በዶፍ ዝናብ በጽናት ቁመዋል፤ ከራስ በፊት ሀገርን አስቀድመዋል።

ውትድርና ለሀገር መስዋዕትነት ነው፤ ውትድርና ከራስ ሕይዎት በላይ ለሀገር መቆም ነው፤ ለሕዝብ ነጻነት መታገል፤ ለሀገር ሉዓላዊነት መዋደቅ ነው። ውትድርና ሰብዓዊነት ነው ራስን ለሕዝብ አሳልፎ መስጠት።

መደበኛ ኾኖ ከተቋቋመ አያሌ ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወጀቡ ሳያናውጠው በጽናት ለክብሯ ዘብ ቁሟል።

ይህ አንጋፋ ተቋም ሠራዊቱን በቴክኖሎጅ የታገዙ መሳሪያዎችን አስታጥቋል፤ የዘመኑን ሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ታቅፏል፤ ከሀገሩ አልፎ ለአፍሪካ ሉዓላዊነት ዘብ ነው። በአየር፣ በምድር፣ በባሕር ኃይል ተጠናክሯል።

ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማፍረስ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችን ልክ ያስገባል። የንጹሐንን ሕይወት የሚቀጥፉ፤ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት የሚያደርሱ፤ ንብረት የሚዘርፉ እና የሚያወድሙ ታጣቂዎች ላይ ሕግ የማስከበር ተግባር ያከናውናል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪ እና የተኩስ አመራር ኀላፊ ሌትናል ጄኔራል ዓለምሸት ደግፌ ከሰሞኑ ከከፍተኛ አመራሮች ጋር ባደረጉት ቆይታ የብሔር ጽንፈኝነት የሀገርን ሰላም እያወከ ይገኛል ብለዋል።

የውጭ ጠላቶች የኢትዮጵያን ሰላም ለማደፍረስ እየሠሩ እንደኾነም አንስተዋል። እኔ ያልመራኋት ሀገር ልትወድም ይገባል ብለው የተነሱ ታጣቂዎች በየቦታው ትንኮሳ መፈጸማቸውን አንስተዋል።

የውስጥ ችግሮችን በውይይት ከመፍታት ይልቅ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ከውጭ ጠላቶች ጋር በመጣመር የራሳቸውን ፍላጎት በሕዝብ ላይ ለመጫን፤ ደም መፋሰስ እንዲቀጥል ለማድረግ እየሠሩ መኾኑን ጠቁመዋል።

ሕወሓት በወጣቶች ላይ ወታደራዊ ግዳጅ በማወጅ እና ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመቀናጀት ዳግም የትግራይ ሕዝብን ስቃይ ለማራዘም እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

በነፍጥ የመፈታተሽ ሂደት ሀገር እያደማ፤ ትውልድ ዋጋ እየከፈለ፤ ከዕድገት ወደ ኋላ እየቀረን፤ ሕዝቦች በድህነት እንዲቆዩ እያደረገ በመኾኑ ከዚህ መውጣት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ከጥፋት ሴራቸው፣ ከተላላኪነታቸው የማይመለሱትን የመከላከያ ሠራዊት በዘመኑ ቴክኖሎጅ ይበልጥ በመደራጀት፤ በቂ ኃይል በመፍጠር፤ ጊዜውን የሚመጥን ትጥቅ በመያዝ ውጤታማ ተግባርን ለማከናወን ዝግጁ ነው ብለዋል።

የመከላከያ ሠራዊት የውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክተር ሜጄር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ በቅርቡ ከሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሠራዊቱ ጠላቶችን እንደ ሰም ለማቅለጥ ዝግጁ መኾኑን ተናግረዋል።

የሀገር የመከላከያ ሠራዊት ጠላቶችን ሳይጀምሩ በመቅደም በእንጭጩ የሚያስቀር ጠንካራ ተቋም ነው ብለዋል። የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመዳፈር የሚመጡ ጠላቶችን በጠንካራ ክንድ ለማድቀቅ መከላከያ ሠራዊት ሁሌም በተጠንቀቅ ላይ መኾኑን ተናግረዋል።

#አሚኮ_ዜና#መከላከያ_ሠራዊት#አማራ_ክልል#ኢትዮጵያ 🇪🇹
#Amhara_Media_Corporation_News #Defense_Forces #Amhara_Region #Ethiopia 🇪🇹

#ባሕር ዳር: #ሰኔ28/2018ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

Previous article“በምርጫ የተገባውን ቃል በላቀ አፈጻጸም ማረጋገጥ ይገባል” አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)
Next article” በድርጊታችን ተጸጽተናል” የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎች