” በድርጊታችን ተጸጽተናል” የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎች

6

 

በሰሜን ወሎ ዞን በራያ ቀጣና የሰላም አማራጭን ከተቀበሉ ታጣቂዎች ጋር ውይይት ተካሂዷል።

የራያ ቆቦ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ መኮነን አጥናፉ መንግሥት ሁለንተናዊ ሰላምን ለማስፈን ከኅብረተሰቡ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ስለ ሰላም እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

በዚህም በወረዳው በተለያዩ አካባቢዎች በጫካ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን እየተቀበሉ እየገቡ መኾናቸውን ተናግረዋል።

የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎችን በተለያዩ የሥራ እድሎች በዘላቂነት ለማቋቋም እንደሚሠራ አንስተዋል። የሰላምን አማራጭ ያልመረጡ ሌሎች የታጠቁ ኃይሎችም ለሀገር እና ለሕዝብ ሰላም ሲሉ የሰላም ጥሪውን እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የቆቦ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ኀይለዓብ ወንድሙ ነፍጥ አንግቦ ጫካ መውጣት ምንም ለውጥ የማያመጣ መኾኑን ተረድታችሁ መንግሥት የሰጠውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ሰላምም መምረጣችሁ አርቆ አሳቢ መኾናችሁን ያሳያል ብለዋል።

በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የመከላከያ ሠራዊት የኮር አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ጧሂር ሳሊህ ሰላምን ለማጽናት በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል።

ወደ ሰላም የመጡ ታጣቂዎች ከሕዝቡ እና ከጸጥታ አካላቱ ጎን በመኾን የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ መሥራት አለባቸው ነው ያሉት።

ሕዝቡ ለሰላም የሚያደርገውን ርብርብ ማጠናከር እንደሚገባውም አመላክተዋል። የታጠቁ ኀይሎች የሰላም በር ሁልጊዜም ክፍት መኾኑን ተረድተው የሰላም አማራጭን መቀበል እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎችም መንግሥት የሕዝቡን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ እንደሚፈታ መገንዘባቸውን ገልጸዋል። ከመንግሥት እና ከሕዝብ ጎን በመሰለፍ ሌሎች ጫካ የሚኖሩ የታጠቁ ኀይሎች ወደ ሰላም ለመመለስ ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል።

በድርጊታቸው መጸጸታቸውን እና ቀጣይ ከመንግሥት ጎን በመኾን ለሰላም እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል። “የበደልነውን ሕዝብ ለመካስ ዝግጁ ነንም” ብለዋል።
ከራያ ቆቦ ወረዳ ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው መንግሥት በተለያዩ የሥራ እድሎች በዘላቂነት እንዲያቋቁማቸውም ጠይቀዋል።

#ሰላም፣ #የሰላምአማራጭ፤#ዘለቂሰላም
#ባሕር_ዳር: ሰኔ 28/2018 ዓ.ም

Previous article🔥 መከላከያ ሠራዊት ዛሬም እንደትናንቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የማጽናት አቋም ላይ ነው”🔥 🇪🇹