ኔቶ የሆርሙዝን የባሕር ሰርጥ በቋሚነት ክፍት ማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ይመክራል 🌐⚓

2

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 24/2018 ዓ.ም የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) በመጪው ሳምንት የመሪዎች ጉባኤን በአንካራ ሊያካሂድ መኾኑን የጀርመኑ ቻንስለር ፍሪድሪክ ሜርዝ ከኔቶ ዋና ጸሐፊ ማርክ ሩት ጋር በበርሊን የጋራ መግለጫ በሰጡበት ወቅት አስታውቀዋል።

ጉባኤው በዋናነት በኅብረቱ የወደፊት አቅጣጫ እና በአትላንቲክ ትብብር ዙሪያ ይመክራል ተብሏል። በመካከለኛው ምሥራቅ እየተከናወኑ ባሉ ጉዳዮች ላይ ይወያያል ተብሎ ይጠበቃል።

በተለይ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል በተጀመረው የዲፕሎማሲ እና የሰላም ጥረት ላይ ትልቅ ትኩረት እንደሚያደርግ መግለጫው አረጋግጧል።

የጉባኤው ዋነኛ ግብ የኢራንን የኒውክሌር ፕሮግራም ማስቆም እና የሆርሙዝን የባሕር ሰርጥ በቋሚነት ክፍት ማድረግ ነው ተብሏል። ይህንኑ የሰላም ጥረት ለማገዝ ጀርመን በቅርቡ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተፈረመውን የ300 ቢሊዮን ዶላር የመልሶ ግንባታ ዕቅድ በገንዘብ ለመደገፍ ዝግጁ መኾኗን ቻንስለሩ አረጋግጠዋል።

የኢራንን የመልሶ ግንባታ ሥራዎች ለማገዝ የተከፈተው በር እውን የሚኾነው ግጭቱ ሙሉ በሙሉ ሲቆም እና አስተማማኝ የተኩስ አቁም ሲረጋገጥ ብቻ ነው ብለዋል።

ከዚህ የሰላም ስምምነት እና ድጋፍ ጀርባ ያለው ዋነኛ ግፊት የአውሮፓን የኢነርጂ ደኅንነት ማረጋገጥ ነው። የፈረሰውን የአካባቢውን መሰረተ ልማት መልሶ መገንባት ለአሕጉሪቱ የኢነርጂ አቅርቦት እጅግ ወሳኝ ነው።

ጀርመን የመልሶ ግንባታውን ለማፋጠን የበኩሏን ሚና እንደምትጫወት ቻንስለሩ ማረጋገጣቸውን አናዶሉ ዘግቧል።

#ኔቶ #መካከለኛው_ምስራቅ #ጀርመን #ኢራን #የሰላም_ስምምነት #NATO #NATOSummit #MiddleEastPeace

በስማቸው አጥናፍ

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በግንቦት እና በሰኔ ወራት ያከናዎኗቸው ተግባራት