ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በግንቦት እና በሰኔ ወራት ያከናዎኗቸው ተግባራት

6

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 24/2018 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በግንቦት እና ሰኔ 2018 ዓ.ም ወራት በጠቅላላ ምርጫ፣ በቱሪዝም፣ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በዲጂታል ኢትዮጵያ፣ በሀገር በቀል ሪፎርም እና ቀጣናዊ ዲፕሎማሲ ዙሪያ ላይ ያተኮሩ የተለያዩ ከፍተኛ የሥራ ክንውኖችን አድርገዋል።

✍️ ጠቅላላ ምርጫ

ግንቦት 24/ 2018 ዓ.ም በተካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በትውልድ ስፍራቸው በሻሻ ወረዳ በመገኘት ድምጻቸውን ሰጥተዋል። በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክትም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እና ለሀገር ፍቅር ላሳየው ቁርጠኝነትና ለከፈለው መስዋዕትነት ታላቅ አድናቆታቸውን ገልጸዋል። ይህንኑ አስመልክቶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሰኔ 14/ 2018 ዓ.ም የምርጫ ውጤቱን በይፋ ያወጀ ሲሆን በተመዘገበው ስኬት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና የሀገራት መሪዎች የደስታ መግለጫና የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክቶችን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አድርሰዋል።

✍️ አረንጓዴ ዐሻራ

የ2018ዓ.ም አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ማስጀመሪያ በሰኔ ወር ተከናውኗል። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በዚሁ ኩነት ላይ ተገኝተው ዐሻራቸውን በማሳረፍ የዚህን ዓመት ሀገር አቅፍ ንቅናቄ አስጀምረዋል። በዚህ ዓመት 8 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል። መርሐ ግብሩ ቀደም ሲል ከታለመለት 48 ቢሊዮን ችግኞች ግብ ወደ 65 ቢሊዮን ችግኞች ከፍ ብሏል። ለዚህም ትልም መሳካት ‘’ተስፋን እንትከል’’ በሚል መሪ መልዕክት በተለያዩ ሀገር አቀፍ ኩነቶች ላይ ዜጎችና መሪዎች በጽናት ዐሻራቸውን በማሳረፍ ላይ ይገኛሉ።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለአየር ንብረት ጥበቃ ከሚያበረክተው መሠረታዊ አስተዋፅዖ ባለፈ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የማር ምርት ላይ ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል። ተፈጥሮን እና አካባቢን በመጠበቅ የደኖች መስፋፋት ተፈጥሯል። ይህም የንብ ማንባትን የሚያግዙና የማር ምርትን የሚያሳድጉ ምቹ ከባቢዎችን በመፍጥር የስርዓተ ምግብ መሻሻልን አረጋግጠዋል።

✍️ ዲጂታል ኢትዮጵያ

የዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞን እውን ለማድረግና ለማፋጠን ተተኪውን ትውልድ ማብቃትን ታሳቢ አድርጎ በሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም የተጀመረው የ”5 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደሮች’ መርሐ ግብር ታቅዶለት ከነበረው የሦስት ዓመታት ጊዜ ቀድሞ ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ መሳካቱን በማስመልከት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ለኢትዮጵያ ሕዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

ወጣት ተማሪዎች መጪውን ክረምት ይህን ታላቅ ዕድል በመጠቀም ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉና ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው የዲጂታል መሪ እንዲኾኑ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

በተመሳሳይም «ዲጂታል ለልህቅት» በሚል ስያሜ የተዘጋጀ ጉባኤ ላይ የተሳተፉት ጠቅላይ ሚንስትሩ በተለያዩ ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን በአንድ መድረክ የሚያጣምረውን በአፍሪካ ተቀዳሚ የኾነውን የ’መሶብ’ የተቀናጀ የዲጂታል አገልግሎት መተግበሪያ በይፋ መርቀዋል። ይህ አገልግሎት የኢትዮጵያ ትልሞች ከተራ ምኞት ባሻገር በዜጎቿ እጆችና አቅም የሚገነባ እውነታ ምስክር ማሳያ ነው ብለዋል።

✍️ የሚንስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ

በሰኔ ወር የሚኒስትሮች ምክር ቤት 56ተኛ እና 57ተኛ መደበኛ ስብሰባ በጠቅላይ ሚንስትሩ መሪነት ተካሂዷል። በ56ተኛ መደበኛ ስበሰባው ላይ ምክር ቤቱ የመካከለኛ ዘመን (2019-2023) የማክሮ ኢኮኖሚና ፊስካል ማዕቀፍ ላይ፣ የ2019 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት የበጀት ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ቁልፍ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።

በተመሳሳይ በ57ተኛ መደበኛ ስብሰባው ላይ በፋይናንስ ድጋፍና ብድር ስምምነቶች፣ የአገልግሎት ተቋማት የአገልግሎት ክፍያ ወሰን፣ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ እና የከተማ ልማት ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።

✍️ ፕሮጀክቶች ጉብኝት እና ምረቃ

በአፍሪካ ታሪክ ግዙፉ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ጥር 2/2018 ዓ.ም መጀመሩ ይታወሳል። ይህም ሲጠናቀቅ በዓመት 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የሚያስተናግደውና የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቅምን በ4 ነጥብ 4 እጥፍ የሚበልጠው ይህ ፕሮጀክት ሀገራችንን ቀዳሚ የአቪዬሽን ማዕከል ያደርጋታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሰኔ 8/2018 ዓ.ም በዚሁ ስፍራ ተገኝተው የፕሮጀክቱን አሁናዊ ሁኔታና አመርቂ የእድገት ምዕራፍ ጎብኝተዋል። በተያያዘም ሥነ-ምህዳርንና የከተማ ግብርናን የሚያቀናጀውን ከእንጦጦ እስከ ቀጨኔ መድኃኔዓለም የመልሶ ማልማት ፕሮጀክት አስጀምረዋል። መዲናችንን የቱሪዝም ማዕከል የሚያደርገውን የ87 ነጥብ 6 ሄክታር የእንጦጦ ቀበና የወንዝ ዳርቻ ልማትን መርቀዋል። በጥራትና ፍጥነት እየተከናወኑ ያሉ የ3D ሕትመትና የኮንቴይነር መኖሪያ ቤቶች ግንባታ አሁናዊ አፈጻጸምንም ተመልክተዋል።

✍️ ዲፕሎማሲ እና የሁለትዮሽ ግንኙነቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ( ዶ.ር) በቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከተመራ የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል። የአፍሪካ ተቋማት በአኅጉሪቱ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ ላላቸው ቁልፍ ሚና የላቀ እውቅና ሰጥተዋል። ይህ የአህጉራዊ ተቋማትን አቅም የማጠናከር ተግባር ወደ ቀጣናዊ ትብብርም በመሻገር፣ ከሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ጋር በሁለትዮሽ ኢኮኖሚያዊ፣ ደኅንነት እና ቀጣናዊ መረጋጋት ዙሪያ ወደ ተደረገ ፍሬያማ ውይይት አምርቷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ አጋጣሚ የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ትስስር ከድንበር ባለፈ በጋራ ሕዝቦች እና በማይነጣጠል እጣ ፈንታ ላይ የተመሰረተ መኾኑን አጽንኦት ሰጥተውታል።

✍️ ከሰኔ ወር ክንዋኔ ውስጥ በ«ኢትዮጵያ ታከናውናለች» የተሰኘ ጉባዔ ላይ ጠቅላይ ሚንስትሩ ተሳትፈዋል። ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ መዋቅር፣ በግብርና፣ በማዕድን፣ በኢንቨስትመንትና መሰል ዓበይት መስኮች ላይ ከለውጥ ባሻገር ወደ ዘላቂ ሽግግር ለመድረስ የወሰደቻቸውን ቆራጥ እርምጃዎችና እምርታዎቻቸው ላይ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል። ጠቅላይ ሚንስትሩም የተገኙት ለውጦች በአጋጣሚ የተገኙ ድሎች ሳይኾኑ ይልቁንም በመደመር መንፈስ ላይ ተመስረተው በጽናት፣ በጋራ በመቆም በተወሰዱ ቆራጥ እርምጃዎች መኾናቸውን ጠቁመዋል። እነዚህን ድሎች ዘላቂ ለማድረግ የጋራ ትብብርና የትውልድ ቅብብሎሽን የሚሻ መሠረታዊ ጉዳይ በመኾኑ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ጥሪ አስተላልፈዋል።

✍️ የክረምቱን መቃረብ ተከትሎም በጎሮ ወረዳ የ20 አዳዲስ ቤቶች ግንባታን የሚያካትተው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘመቻ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጀምሯል። እነዚህን ግዙፍ መሠረተ ልማቶች ከሀገራዊ ንቅናቄው ጋር በማስተሳሰር፣ የሚሠራ እጅ፣ የሚናገር አፍ እና የሚያስብ አእምሮ የተናበቡበት ስኬታማ ታሪክ በወሩ ተመዝግቧል።

✍️ የግንቦትና ሰኔ 2018ዓ.ም አጋማሽ ክንዎኖች በቱሪዝም ውይይት የተጠናቀቀ ነው። በዚህ ቃለ መጠይቅ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ቱሪዝም ዋነኛ የኢኮኖሚ ዘርፍ ብቻ ሳይኾን የኢትዮጵያ ማንነት ነጸብራቅም መኾኑን ገልጸዋል። የቅርስ አጠባበቅ ላይ የተደረጉ ለውጦችን እና የተፈጥሮ ተስማሚ የኩነት ቱሪዝም መስፋፋትን አንስተዋል። እነዚህም የጎብኚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በዚህም ኢትዮጵያ በዘንድሮው ዓመት 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ጎብኚዎችን አስተናግዳ ከ5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የቱሪዝም ገቢ አግኝታለች።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleሠራዊቱ ለሕዝብ የቆመ የሰላም አምባሳደር ነው።
Next articleኔቶ የሆርሙዝን የባሕር ሰርጥ በቋሚነት ክፍት ማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ይመክራል 🌐⚓