የኢትዮጵያውያንን ፍላጎት እና ተስፋ የያዘው ምክክር

5

 

#ባሕር _ዳር: ሰኔ 24/2018 ዓ.ም 🇪🇹 የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የምክክሩን አካታችነት እና አሳታፊነት ለማረጋገጥ ሰፋፊ ሥራዎችን አከናውኗል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ምክክሩን አሳታፊ እና አካታች ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ ሰፋፊ ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል።

የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን፣ የሃይማኖት ተቋማትን፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን፣ ማኅበራትን፣ ታዋቂ ሰዎችን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እና በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በማካተት አሳታፊ ተደርጓል ነው ያሉት።

እንደ ዋና ኮሚሽነሩ ማብራሪያ በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች ተደራሽ በመኾን በተሳካ ሁኔታ አጀንዳዎችን የማሠባሠብ እና ወካይ ተሳታፊዎችን በመለየት እንዲካተቱ ተደርጓል።

ማኅበራትን፣ አደረጃጀቶችን እና ተቋማትን በመጠቀም የሀገር ሽማግሌዎችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ ምሁራንን፣ ሴቶችን፣ ወጣቶችን፣ ሠራተኞችን እና ተፈናቃዮችን ጨምሮ ሁሉም አካላት እኩል ተሳትፎ እንዲኖራቸው መደረጉንም አረጋግጠዋል።

በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይወሰን በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንንም በሂደቱ ማሳተፍ እንደተቻለ ገልጸዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ከልሂቃን፣ ከመሪዎች እና ከምሁራን ጋር ቁጭ ብለው ስለሀገራቸው የሚወያዩበት ታሪካዊ መድረክ መኾኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ ዘላቂ ሰላም፣ ሀገራዊ መግባባት እና የጋራ እጣ ፋንታ በጋራ መበየን አስፈላጊ በኾኑበት ታሪካዊ መስለቀኛ መንገድ ላት ትገኛለች ያሉት ፕሮፌሰሩ
ለዚህም ምላሽ ለመስጠት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሞሽን አካታች እና አሳታፊ ሂደትን መከተሉን ገልጸዋል። በሂደቱ የተዋጣ ሥራ መሥራቱን ገልጸዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የመረጣቸው ስምንቱ ዋና ዋና ሀገራዊ አጀንዳዎች ከኢትዮጵያ ሕዝብ የተቀዱ ናቸው ብለዋል። የሀገራዊ አጀንዳ ልየታን አካታችነት፣ አሳታፉነት እና ታማኝነት ለማረጋገጥ በትኩረት መሥራቱን ገልጸዋል። የኢትዮጵያውያን ፍላጎት፣ ስጋት እና ተስፋ በአጀንዳዎቹ መካተቱን ተናግረዋል።

እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለኢትዮጵያ አስተዋጽኦ እንዳለው በሂደቱ መታየቱን ገልጸዋል።

ዛሬ ላይ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በርካታ ሂደቶችን አልፎ ስለኢትዮጵያ ለመምከር ለሐምሌ 08/2018 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል።

#አሚኮ_ዜና #የሀገራዊ_ምክክር #ኢትዮጵያ #EthiopianNationalDialogue

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article📢 በምክክር ሀገር አንድነቷን ታስጠብቃለች፣ ሰላሟን ታረጋግጣለች