📢 በምክክር ሀገር አንድነቷን ታስጠብቃለች፣ ሰላሟን ታረጋግጣለች

2

 

#ባሕር ዳር: ሰኔ 24/2018 ዓ.ም ኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የምታደርግበት ቀን ተቆርጦ ምክክር የሚደረግባቸው መሠረታዊ አጀንዳዎችም ተለይተዋል።

ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን ዓርአያ በሰጡት ማብራሪያ ላለፉት አራት ዓመታት ከ2 ሺህ በላይ አጀንዳዎች እንደተሰበሰቡ ተናግረዋል። ከታች ጀምሮ ከተሰበሰቡት አጀንዳዎች መካከል ለግጭት እና ለጦርነት ምክንያት የኾኑትን ስምንት መሠረታዊ አጀንዳዎች ለይቶ ምክክር እንዲደረግባቸው ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመወያየት ያልተመረጡ አጀንዳዎች አይጣሉም ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ በክልል ደረጃ የሚፈቱት ለ12ቱ ክልሎች እና ለ2ቱ ከተማ አሥተዳደሮች ተለይተው ምላሽ እንዲሰጡባቸው፤ ቅርብ በሚባል ጊዜ በትናንሽ መጻሕፍት ተሰንደው ይላካሉ ነው ያሉት።

የተሠበሠቡ ሁሉም የሕዝብ አጀንዳዎች ቀጣዩ ትውልድ የወላጆቻቸውን ጥያቄዎች እና የመከሩባቸውን ጉዳዮች እንዲያውቁ እና ለምርምር እንዲጠቀሙባቸው ተሰንደው በቴክኖሎጂ ዲጂታላይዝድ ኾነው እንዲቀመጡ ተደርጓል ብለዋል።

በስምንቱ አጀንዳዎች ላይ የሚደረገው የምክክር ሂደት በዕውቀት፣ በአመክንዮ፣ በመደማመጥ እና በመከባበር ላይ የተመሠረተ ስምምነት ላይ የመድረስ እንጂ ተከራክሮ የማሸነፍ ጉዳይ እንዳልኾነም አንስተዋል።

ምክክሩ ከስሜታዊነት ወጥቶ እና ምክንያታዊ ኾኖ አንደኛው የሌለውን ሕመም የሚረዳበት እንደሚኾን አስገንዝበዋል። ኢትዮጵያውያን እየመከሩ ነው እዚህ የደረሱት፣ መመካከር የግድ ያስፈልጋል ብለዋል።

ሐምሌ 08/2018 ዓ.ም ደግሞ ታላቁ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በአዲስ አበባ ኮንቬንሽን ማዕከል ይጀምራል ብለዋል። በምክክሩ 130 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ ሃይማኖቶች፣ ፖለቲከኞች እና ዲያስፖራዎች የተወጣጡ 4 ሺህ ተሳታፊዎች በጉባኤው ላይ ይሳተፋሉ ነው ያሉት።

አመካካሪዎች ቀደም ሲል ከኔዘርላንድ እና ከስዊድን በመጡ አሠልጣኞች ሥልጠና እንደተሰጣቸውም አመላክተዋል።

የምክክር ሂደቱ ቢያንስ ለ30 ቀናት ይቆያል ያሉት ዋና ኮሚሸነሩ ለምክክሩ ለተሳታፊዎች ማረፊያ፣ ሕክምና፣ የሕጻናት ማቆያ፣ መስገጃዎች እና ሌሎች ሎጀስቲኮች ተዘጋጅተዋል ብለዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድም ለሀገር ሲባል ለተሳታፊዎች የትራንስፖርት ዋጋ ቅናሽ እንዳደረገላቸው ገልጸዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደርም ትልቅ እገዛ እያደረገ መኾኑን ጠቅሰዋል።

የምክክር ሂደቱ አሰልቺ እንዳይኾን ጎን ለጎን አዲስ አበባ ላይ የተለያዩ ሁነቶች እንደሚኖሩም አመላክተዋል።

በምክክር ሀገር ትሻገራለች፤ ሰላሟን ታረጋገጣለች፤ ኢትዮጵያውያን ችግሮቻቸውን በራሳቸው ለመፍታት አጀንዳዎቻቸውን መርጠዋል፤ ለምክክር ቀን ቆርጠዋል፤ በቀደመ ብልሃታቸው፤ ሀገር በማጽናት ጥበባቸው ችግሮቻቸውን በምክክር ይፈታሉ። የጋራ መፍትሔ ያስቀምጣሉ።

#የሀገራዊምክክር #ኢትዮጵያ #ሰላምናመግባባት #NationalDialogue #EthiopianDialogue #PeaceAndReconciliation

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

Previous article🌱 የአረንጓዴ አሻራ ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶች ከተፈጥሮ ጥበቃ እስከ ኢኮኖሚያዊ ልዕልና 🌳🥑🐝📈
Next articleየኢትዮጵያውያንን ፍላጎት እና ተስፋ የያዘው ምክክር