🌱 የአረንጓዴ አሻራ ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶች ከተፈጥሮ ጥበቃ እስከ ኢኮኖሚያዊ ልዕልና 🌳🥑🐝📈

0

 

#ባሕር_ዳር: ሰኔ 24/2018 ዓ.ም የደን መመናመን ለኢትዮጵያም ኾነ ለአፍሪካ የረጅም ጊዜ ፈተና ኾኖ ቆይቷል። አህጉሪቱ በዓመት 3 ነጥብ 94 ሚሊዮን፣ ኢትዮጵያ ደግሞ 72 ሺህ ሄክታር ደን በየዓመቱ ስታጣ ኖራለች። የደን መራቆት ለድህነት እና ለግብርና ምርት መቀነስ ዋነኛ መንስኤ ነው።

እንደ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር ጥናት የደን ሀብት ለገጠር ማኅበረሰብ የዕለት ተዕለት ኑሮ ወሳኝ ነው። ሕዝቡ ለምግብ፣ ለማገዶ፣ ለንብ ማነብ፣ ለቡና እና ለመድኃኒት በደን ላይ ጥገኛ ነው።

አንድ አባወራ ከአጠቃላይ ዓመታዊ ገቢው ከ10 እስከ 60 በመቶ የሚኾነውን ከደን እንደሚያገኝ ጥናቱ አረጋግጧል። በአንጻሩ ደን ለሀገራዊ ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ አነስተኛ ግምት ይሰጠዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ፕሮግራም ጥናት የደንን እውነተኛ የኢኮኖሚ አስተዋጽኦ 13 በመቶ እንደኾነ ያሳያል። ግምቱ ዝቅተኛ የኾነው በመረጃ አያያዝ ክፍተት እና ትክክለኛ የግምት ማውጫ ስልት ባለመኖሩ እንደኾነ ተመላክቷል።

ኢትዮጵያ ከዚህ አሳሳቢ ችግር በፍጥነት ለመውጣት፣ የደን ልማትን ምጣኔ ሀብታዊ አስተዋጽኦም ለማሳደግ በ2011 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራነረ በመውጫነት ለመተግበር እንቅስቃሴ ጀምራለች።

እስካሁን 48 ቢሊዮን ችግኞች በመተከላቸው የሀገሪቱ የደን ሽፋን 23 ነጥብ 6 በመቶ ደርሷል። በዚህም 12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት እንዲያገግም መደረጉን ግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።

አረንጓዴ አሻራ ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ጭምር አንድ ቢሊዮን ችግኞችን በማካፈል አህጉራዊ ትብብርን ያጠናከረችበት እንደኾነ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር ጥናት ያሳያል። በዚህም ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ትልቅ ፋይዳ እንደሚያበርክትም ይታመናል።

አረንጓዴ አሻራ ከሥነ ምኅዳር ጥበቃ ባሻገር ግዙፍ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር ኾኗል። ወጣቶች በንብ ማነብ፣ በአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ተሰማርተው ተጠቃሚ እንዲኾኑ አስችሏቸዋል። ግብርና ሚኒስቴር ለዚህ አብነት የሚያደርገው 197 ሺህ 843 የማኅበረሰብ ተፋሰሶች በዘላቂነት በልማት ላይ መኾናቸውን ነው።

የአፈር መሸርሸር በመቀነሱ እና የውኃ ተፋሰሶች በመጠበቃቸው አጠቃላይ የግብርና ምርታማነትም አድጓል። በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ውጤታማ መኾን የተቻለውም የደን ልማቱ እያበረከተ ባለው የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ ነው።

ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ሁለተኛዋ የአቮካዶ ላኪ የኾነችው ከአረንጓዴ አሻራ ትኩረት በኋላ መኾኑ ፋይዳውን ከፍ ያደርገዋል። አሁንም የአቮካዶ ልማትን በማስፋፋት ዓመታዊ ምርትን ወደ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ቶን ለማሳደግ ትልቅ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ የብሔራዊ አቮካዶ ፕሮግራም መረጃ ያሳያል።

አረንጓዴ አሻራ የዕፅዋት ጥግግት እና ብዝኀነት ለንቦች የተትረፈረፈ ምግብ እና ምቹ መኖሪያ መፍጠሩን በሆለታ ንብ ማነብ ምርምር ማዕከል የተሠራው እና በኢትዮጵያ የንብ ልማት ማኅበር ይፋ የተደረገው ጥናት ያሳያል።

እንደ ጥናቱ በኢትዮጵያ 62 ነጥብ 2 በመቶ የሚኾኑት ዋና ዋና ሰብሎች በነፍሳት ማዳቀል ላይ ጥገኛ ናቸው። በ2015/16 የምርት ዘመን በኢትዮጵያ የዚህ አገልግሎት ኢኮኖሚያዊ እሴት 814 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር እንደነበርም ጥናቱ አረጋግጧል።

እንደ ጥናቱ የንብ ማነብ ቴክኖሎጂን ከደን ጥበቃ ጋር ማዋሃድ የማር ምርትን በአራት እጥፍ አሳድጓል። ገቢንም በ5 ነጥብ 76 እጥፍ ከፍ አድርጎታል። በተጨማሪም ይህ ተግባር የንብ መኖ የኾኑ ዕፅዋት ልማትን ያበረታታል። በዚህም ለደን አያያዝ እና እንክብካቤ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።

ሀገራዊው የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ተፈጥሮን ከማዳን አልፎ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በዘላቂነት እያረጋገጠ የሚገኝ ስኬታማ ጉዞ ነው።

#አሚኮ_ዜና #GreenLegacyEthiopia

ዘጋቢ፦ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleትምህርት ቤቶቹ ታግደዋል?
Next article📢 በምክክር ሀገር አንድነቷን ታስጠብቃለች፣ ሰላሟን ታረጋግጣለች