
ባሕር ዳር:ሰኔ 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በ2018 ዓ.ም ያስተምሩ ከነበሩ ትምህርት ቤቶች መካከል ሦስቱ መታገዳቸው በማኅበራዊ ሚዲያ ተሠራጭቷል።
👉እውነት ነውን?
-የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት ምሪያ ኅላፊ ሙሉዓለም አቤ(ዶ.ር) ልክ ነው ለ2019 የተምህርት ዘመን እንዳያስተምሩ የታገዱ ትምህርት ቤቶች አሉ ብለዋል።
👉ትምህርት ቤቶቹ እነማን ናቸው?
-ሪስፔንስ ሁለተኛ ደረጃ
-ሐመር ቁጥር 1 እና
-አቡነ ጎርጎሪዮስ አንደኛና መካከለኛ ትምህርት ቤቶች መኾናቸውን ገልጸዋል።
👉ለምን ታገዱ
-ሪስፔንስ ሁለተኛ ደረጃ፦ እንደ ዶክተር ሙሉዓለም ገለጻ ይህ ትምህርት ቤት ከስታንዳርድ በታች በመኾኑ በፌዴራል ደረጃ የማስተማር ፈቃዱ ተነስቶበታል።
በ2018 ዓ.ም ማስተማር አልነበረበትም ያሉት ኃላፊው ነገር ግን በድብቅ ተማሪዎችን መዝግቦ በመገኘቱ እና የተማሪዎች እና የወላጆችን መጉላላት ለማስቀረት ሲባል ዓመቱን እንዲያስተምር ተደርጓል ብለዋል።
ይሄንንም ትምህርት መምሪያው ለወላጆች ማሳወቁን የገለጹት መምሪያ ኀላፊው ከዚህ በኋላ ትምህርት ቤቱ በመማር ማስተማር ሥራ እንደማይቀጥል ስላሳወቅን ትምህርት ቤቱ ተዘግቷል ብለዋል።
👉ሐመር ቁጥር 1፦ በ2018 የትምህርት ዘመን በማስጠንቂያ ሲያስተምር መክረሙን ነው ዶክተር ሙሉዓለም ያነሱት። ስፖርት ሜዳ አለመኖር፣ ክፍሎች ለመማር ማስተማር ተብለው የተሠሩ አለመኾን፣ ለለህጻናት ደህንነት የማይመች አስፋልት ዳር በመኾኑና በመሰል ችግሮች አኹን ባለበት ቦታ የማስተማር ፈቃዱ ታግዷል።
አቡነ ጎርጎሪዮስ አንደኛና መካከለኛ ትምህርት፦ ይህ ትምህርት ቤት እንደ ሐመር ቁጥር 1 ሁሉ በ2018 ሲያስተምር በከረመበት ቦታ እንዳይቀጥል የታገደ መኾኑን መምሪያ ኅላፊው ገልጸዋል።
አስፋልት ዳር መኾኑ እና ህንጻዎቹ ለመማር ማስተማር ተብለው የተሠሩ ባለመኾናቸው በቦታው መቀጠል አይችልም ብለዋል።
ትምህርት ቤቶቹ ያሉበትን ኹኔታ ለባለሃብቶችም ለወላጆችም ግንዛቤ መፈጠሩን የጠቀሱት ዶክተር ሙሉዓለም ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያስመዘግቡ የትምህርት ቤቶች ፈቃድ መኖር እና አለመኖሩን ማረጋገጥ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
👉በተጨማሪም በየትኛውም ትምህርት ቤት ከሐምሌ 15 በፊት ልጆችን እንዳያስመዘግቡ እና ለመመዝገቢያም ከ25 በመቶ በላይ እንዳይከፍሉ አሳስበዋል።
ለወላጆች እፎይታ ሲባል እስከ ሐምሌ 15 ትምህርት ቤቶች መመዝገብ የለባቸው ያሉት ኅላፊው ከዚህ በፊት የሚደረግ ምዝገባ በትምህርት መመሪያው ዕውቅና እንደሌለው ገልጸዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
