በክረምት ሊከሰቱ የሚችሉ የጎርፍ አደጋዎችን ለመከላከል እየተሠራ ነው።

1

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 24/2018 ዓ.ም በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አየሁ ጓጉሳ ወረዳ የቻጃ ሚካኤል ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ከፋለ መሠረት እና ታገለ ይሁን በአካባቢያቸው “አንኩሪ” ተብሎ የሚጠራ ወንዝ ክረምት በመጣ ቁጥር በሰው ሕይወት እና በእንስሳት ላይ ጉዳት ያደርስ እንደነበር ገልጸዋል።

ከዚህ ባሻገር ከ50 እስከ 60 ሄክታር መሬት ላይ የተዘራ ሰብል ሙሉ በሙሉ ሲያወድም ቆይቷል ብለዋል።

ዘንድሮ ግን መንግሥት ችግራቸውን ተረድቶ የጎርፍ መከላከያ ሠርቶ በማጠናቀቁ በአሁኑ ወቅት በጎርፍ ተጠርጎ ይሄድ የነበረ ሰብል በጥሩ ቁመና ላይ እንደኾነ ተናግረዋል። ይህን በመመልከታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች የጎርፍ መከላከያ ሥራው ሲሠራ በጉልበት እና በገንዘብ ማገዛቸውንም ገልጸዋል።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሰርካለም አያሌው ለአሚኮ እንደገለጹት የክረምት መግባትን ተከትሎ በአየሁ ጓጉሳ ወረዳ ቻጃ ሚካኤል ቀበሌ ላይ አንኩሪ ተብሎ የሚጠራ ትልቅ ወንዝ የሚፈጥረውን ጎርፍ ለመከላከል የሚያስችል ግንባታ በክልሉ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እና በአውሮፓ ኅብረት የገንዘብ ድጋፍ በ8 ሚሊዮን 532 ሺህ ብር ወጭ መሠራቱን ተናግረዋል።

ሥራው 3ሺህ 969 አባወራ እና አማወራ አርሶ አደሮችን፣ ከ170 ሄክታር በላይ የእርሻ ማሳ እና የግጦሽ መሬት ማዳን መቻሉንም ገልጸዋል። የአካባቢው ማኅበረሰብም ከ2ሚሊዮን በላይ ብር የሚገመት ተሳትፎ አድርጓል ነው ያሉት።

በቀጣይም ከክረምት ጋር ተያይዞ በሚከሰቱ አደጋዎች ተጎጂ የሚኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ የሚያስችሉ ሥራዎች ቀድመው በየአካባቢው እየተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።

በአማራ ክልል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ እና አደጋ ሥጋት ቅነሳ ዳይሬክተር ከፍያለው ጎላ በ2018 ዓ.ም የክረምት ወራት 346ሺህ 895 የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ 60ሺህ 837 ሄክታር የሰብል ማሳ፣ 47ሺህ 147 ሄክታር የግጦሽ መሬት፣ በእንስሳት እና መኖሪያ ቤቶች ጉዳት ሊደርስ ይችላል በሚል ተለይተው ጉዳቱን ለመከላከል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ የበለጠ ተጋላጭ በኾኑ በ9 ዞኖች እና በ18 ወረዳዎች 146 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ከአውሮፓ ኅብረት እና ከመንግሥት በተገኘ በጀት የተለያዩ የጎርፍ መከላል ተግባራት መከናዎናቸውን ገልጸዋል።

በጎርፍ ምክንያት በየዓመቱ በእርሻ መሬቶች፣ በሰብሎች፣ በመኖሪያ ቤቶች እና በመንግሥት ተቋማት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል ከመንግሥት ኘሮጀክት በተጨማሪ ማኅበረሰቡን በማሳተፍ መሠራቱን ተናግረዋል።

የተሠራውን ሥራ ባለቤት እንዲኖረው ርክክብ በማድረግ በዘላቂነት እንዲጠበቅ ክትትል እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

በጎርፍ አደጋ የተጎዱ የእርሻ መሬቶችን ማዳን በመቻሉ አርሶ አደሮች ተገቢውን የግብርና ሥራቸውን በማከናወን ማምረት ችለዋል ያሉት ዳይሬክተሩ በጎርፍ አደጋ ተጎድቶ የነበረ የቦረቦር መሬትን በተለያዩ የጎርፍ መከላከል ግንባታዎች በመታገዝ አሁን ላይ የአትክልት እና ፍራፍሬ ማሳዎች ኾነዋል ብለዋል።

#አሚኮ_ዜና #የጎርፍ_አደጋ #አማራ_ክልል

ዘጋቢ፦ሰለሞን ስንታየሁ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!።

Previous articleበውይይት ያተረፈ እንጅ የከሰረ የለም።