በውይይት ያተረፈ እንጅ የከሰረ የለም።

2

 

#ሰቆጣ: ሰኔ 24/2018 ዓ.ም ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አንጻራዊ ሰላም ካላቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች መካከል አንዱ ነው።

ነገር ግን በሕገወጡ ሕወሃት እና በተላላኪዎች እየተፈጠረ ባለ ትንኮሳ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ አንዳንድ ወረዳዎች የጸጥታ ችግር ተፈጥሯል። ነዋሪዎችም ለእንግልት እየተዳረጉ ነው። በተፈጠረው የጸጥታ ችግር የአብርገሌ ወረዳ እና የጻግቭጅ ወረዳ ነዋሪዎች ከቀያቸው የመፈናቀል ችግር ገጥሟቸዋል። ነዋሪዎች ቀያቸውን ለቅቀው በሰቆጣ ከተማ ለመኖር ተገድደዋል።

ይህንን የሰላም እጦት በውይይት እና በሀገር ሽምግልና መፍታት እንደሚገባ አቶ ሻንበል ከፍያለው እና አቶ በላይ ሹምየ ተናግረዋል።

የጦርነትን ክፋት ባለፉት ዓመታት አይተናል ያሉት ነዋሪዎቹ ከባለፈው ስህተት ባለመማር ዛሬም ሕዝብን ማፈናቀል አይገባም ነው ያሉት። ልዩነትን በሰላማዊ ውይይት እና ምክክር መፍታት ትርፋማ እንጂ ተጎጅ አያደርግም ብለዋል።

ለዚህም የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በጋራ መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጌትነት እሸቱ የዋግን ሰላም ለመጠበቅ የአካባቢው ማኅበረሰብ ከጸጥታ መዋቅሩ ጎን በመሰለፍ እየሠራ ያለው ተግባር የሚበረታታ መኾኑንም ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ የሰላም ስምምነቶችን በመጣስ የሚደረጉ ትንኮሳዎች ሕዝቡን ለእንግልት ዳርጎታል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው መንግሥት አሁንም በሆደ ሰፊነት ለሰላም እጁን እንደዘረጋ ነው ብለዋል።

የሀገርን ሰላም ለማጽናት አሁንም የሰላም ጥሪ እናቀርባለን ብለዋል። ታጣቂ ኀይሎችም ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት የሀገርን ውስጣዊ አንድነት ማጠናከር እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ምክትል ኀላፊ ጌታወይ አብርሃ በዋግ ኽምራ ያለውን ሰላም ለማጽናት መንግሥት የሰላም አማራጮችን እየተከተለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በቀረበው የሰላም አማራጭ በርካታ ታጣቂዎች ለሰላም መግባታቸውን ተናግረዋል። አሁንም ወደ ሰላም በመመለስ የማኅበረሰቡን እንግልት መቀነስ እና የሀገርን አደራ መወጣት ይገባል ብለዋል።

የሀገርን ሰላም ለማጽናት አሁንም የሰላም ጥሪ እናቀርባለን ያሉት አቶ ጌታወይ ታጣቂ ኀይሎች ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት የሀገርን ውስጣዊ አንድነት እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል።

#አሚኮ_ዜና #ሰላም #ዋግኽምራ #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ

ዘጋቢ ፦ደጀን ታምሩ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“ፅንፈኞችን በመምታት የታሪካዊ ጠላቶቻችንን ሀገር የማፍረስ ሴራ እያከሸፍን ነው” ሌተናል ጀነራል መሐመድ ተሰማ
Next articleበክረምት ሊከሰቱ የሚችሉ የጎርፍ አደጋዎችን ለመከላከል እየተሠራ ነው።