
#ባሕር ዳር: ሰኔ 24/2018 ዓ.ም
የምሥራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌ/ጀነራል መሐመድ ተሰማ ፣ የኮር አዛዥ ብ/ጀነራል አዲሱ መሐመድ ፣ የኮር አዛዥ ብ/ጀነራል መላኩ ገላነህ በቋሪት እና በገነት አቦ የተሠማራውን ሠራዊት ተመልክተዋል።
በነበሩት አራት የተለያዩ መድረኮች ላይ ሌ/ጀነራል መሐመድ ተሰማ የውጭ ኀይሎች የተሻለች ኢትዮጵያ እንዳትኖር የሚያደርጉትን ዘርፈ ብዙ ጥቃት ማስቆም የምንችለው የነሱን ተላላኪዎች በመደምሰስ ነው ብለዋል።
በየጥሻው ተሰግስገው የሕዝብ ሰላም የሚያደፈርሱትን እና ሰላምን እና ልማትን የሚያደናቅፉ የጥፋት መልዕክተኞችን በመደምሰስ፣ ለፅንፈኛው ግዳጅ እና ገንዘብ በመስጠት ጦር የሚያዘምቱትን ታሪካዊ ጠላቶችን ሴራ ማክሸፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኮር አዛዥ ብ/ጀነራል አዲሱ መሐመድ ምሥራቅ ዕዝ በየዘመናቱ ኢትዮጰያ በፈለገችው ቀጣና እየተገኘ ክብሯን ያስጠበቀ ዕዝ መሆኗን ገልጸዋል።
አሁንም የፅንፈኛውን ሀገር የማፍረስ ዕቅድ በማክሸፍ የተስተጓጎለውን የአማራ ክልል ሰላም እና ልማት መልሶ እንዲጠናከር በማድረግ የተለመደ ጀግንነቱን መቀጠሉን ተናግረዋል።
የኮር አዛዥ ብ/ጀነራል መላኩ ገላነህ ምሥራቅ ዕዝ ሀገራዊ ተልዕኮውን ከሕዝብ፣ እና ከጸጥታ ኀይል ጋር ተቀናጅቶ በመፈፀም ሰላም የማረጋገጥ እና ሕግ የማስከበር ግዳጁን በብቃት መወጣቱን አረጋግጠዋል።
ሠራዊቱ ይህንን ተላላኪ የሕዝብ ጠላት በፍጥነት በማጥፋት የመደበኛ ግዳጅ ዝግጅት ለማድረግ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል። ዘገባዉ የምሥራቅ ዕዝ ነው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
