
#ባሕር ዳር: ሰኔ 23/2018 ዓ.ም የምሥራቅ እዝ ለሁለተኛ ጊዜ በብር ሸለቆ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ያሠለጠናቸውን መሠረታዊ ወታደሮች አስመርቋል፡፡
ሥልጠናው መሠረታዊ ወታደሮች በማሠልጠኛ ያገኙትን ዕውቀት በተግባር ወደሚታይ እና ወደሚጨበጥ ከፍተኛ ወታደራዊ ክህሎት የሚለውጥ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ጠቃሚ እና የውጊያ ልምድ እንዲያገኙ፤ ሠራዊቱን ይበልጥ ብቁ አስተማማኝ እና ሁል ጊዜም ለድል ዝግጁ የሚያደርግ ነው ተብሏል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የምሥራቅ እዝ ዋና አዛዥ ሌትናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ምሥራቅ እዝ ገናና ታሪክ እና በሕገ መንግሥት የምትመራ ሀገራችንን እያጸና የመጣ ጀግና እዝ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያን እድገት እና ብልጽግና የማይመኙ የውስጥ እና የውጭ ኃይሎች ሲከፍቱ የነበረውን ተደጋጋሚ ጥቃት ከሌሎች የሠራዊት ክፍሎች ጋር በብቃት እየመከተ ኢትዮጵያን ያጸና እዝ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡
ምሥራቅ እዝ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና ልማትን ለማስተጓጎል የሞከሩትን የጥፋት እጆች ሁሉ እየቆራረጠ ከሕዝብ ጎን መኾኑን በተደጋጋሚ ያስመሰከረ እዝ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
የዛሬ ተመራቂዎችም ጀግኖች በየዘመናቱ መስዋዕትነት እየከፈሉ ያቆዩዋትን ኢትዮጵያን አስጠብቀው የማስቀጠል ኀላፊነት እንደተጣለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በ50 ዓመት ዕድሜው ጀግኖችን እያፈራ፣ ታሪክ እየሠራ፣ በየዘመናቱ በዕሳት እየተፈተነ የድል አውራ ወደኾነው እዝ እንኳን መጣችሁ ብለዋቸዋል። ወደ እዙ ስትቀላቀሉ ተሞክሮውን በመቅሰም የጀግንነት ባሕሉን እንደምታስቀጥሉ አምናለሁ ነው ያሉት፡፡
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የእዙ ማሠልጠኛ አዛዥ ኮሎኔል አሊ ሰይድ የሥልጠና ሪፖርት አቅርበዋል። ሠልጣኞች በሥልጠናው ያገኙትን ክህሎት ለክብር እንገዶች በተግባር አሳይተዋል። አድናቆትም ተችሯቸዋል፡፡
በዚሁ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ጄኔራል መኮንኖች፣ ኮር አዛዦች፣ የብር ሸለቆ ውትድርና ማሠልጠኛ አዛዥ፣ የምሥራቅ እዝ ማሠልጠኛ አዛዥ፤ የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳደር አካላት፣ የምሥራቅ እዝ ስታፍ መሪዎች እና የማሠልጠኛው ማኅበረሰብ አካላት ተገኝተዋል፡፡
መረጃው የመከላከያ ሠራዊት ነው።
