የአዋሽ-ኮምቦልቻ- ሃራ ገበያ ባቡር መስመር ጥገናን በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው።

6

 

#ባሕር_ዳር : ሰኔ 23/2018 ዓ.ም
የአዋሽ-ኮምቦልቻ- ሃራ ገበያ ባቡር መስመር ፕሮጀክት ጥገናን በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታውቋል።

የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከፍተኛ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በቅርቡ የጥገና ስራው የተጀመረውን የአዋሽ-ኮምቦልቻ- ሃራ ገበያ የባቡር መስመር ፕሮጀክትን ዛሬ ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር ኅሊና በላቸው እንደገለፁት በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጦ የነበረውን የባቡር መስመር የጥገና ስራን በጥራትና በፍጥነት ገንብቶ ለአገልግሎት ለማብቃት በተለየ ቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዛሬው እለትም የኮርፖሬሽኑ የሥራ አመራር የጥገና ሥራ ያለበትን ደረጃ በአካል ተገኝቶ በመመልከት የቀጣይ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ተናግረዋል።

ኅብረተሰቡም የባቡር መስመር ፕሮጀክቱን ሃብትና ንብረት በመጠበቅና በግንባታ ስራው የራሱን አሻራ በማሳረፍ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ ኢንጅነር ብርሃኑ ተስፋዬ በበኩላቸው የፕሮጀክቱ ጥገና ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ መንግስት በተለየ ትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።

የፕሮጀክቱ ጥገናም በቀጣይ የአካባቢውን ኢኮኖሚ በማነቃቃትና ለአገር እድገት መሰረት በመሆን የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ እንደሆነም አብራርተዋል።

አዋሽ- ኮምቦልቻ- ሃራ ገበያ ባቡር መስመር ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ዳንኤል ኪዳነማሪያም፤ የፕሮጀክቱ የጥገና ሥራ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ከአዋሽ -ኮምቦልቻ -ሃራ ገበያ 392 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን ፕሮጀክት በአራት አቅጣጫ የጥገና ሥራው እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ የካምፖች፣ የሀዲድ መስመርና የባቡር ጥገና እየተካሄደ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።

ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ ጠግኖ ለማስረከብ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

በጉብኝቱ የኮርፖሬሽኑና የኮምቦልቻ ከተማ አመራሮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

#አሚኮ_ዜና #የአዋሽ_ኮምቦልቻ_ሃራገበያ #ባቡር_መስመር #ኢትዮጵያ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!።

Previous article🇪🇹 በሀገራዊ ምክክር ከግጭት አዙሪት ወደ ዘላቂ ሰላምና የሀገር ግንባታ 🕊️🤝
Next article“ተመራቂዎች የጀግንነት ባሕሉን እንደምታስቀጥሉ አምናለሁ” ሌትናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ 🇪🇹