🇪🇹 በሀገራዊ ምክክር ከግጭት አዙሪት ወደ ዘላቂ ሰላምና የሀገር ግንባታ 🕊️🤝

7

 

#ባሕር ዳር: ሰኔ 23/2018 ዓ.ም ሀገራዊ የምክክር መድረኮች ሁሉን አቀፍ እና አሳታፊ የድርድር መንገዶች ናቸው። የፖለቲካ ቀውሶችን ይፈታሉ፤ ለሰላማዊ የፖለቲካ ሥርዓት መንገድ ይከፍታሉ። የረዥም ጊዜ የግጭት መንስኤዎችን ከስር መሰረቱ ለመፍታት ይረዳሉ።

📌 ኢትዮጵያም ከግጭት አዙሪት ለመውጣት ይህንኑ መፍትሔ መርጣለች። ባለፉት አራት ዓመታት በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ አማካኝነት የችግሮች መንስኤ ሲጠኑ ቆይቷል። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊም በሂደቱ ሀሳቡን ሲሰጥ ቆይቷል። በዚህም ከሁለት ሺህ በላይ አጀንዳዎች መሠብሠባቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያሳያል።

📅 በመጭው ሐምሌ 8/2018 ዓ.ም ደግሞ ዋናው የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ይካሄዳል። በምክክሩም የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚወክሉ አራት ሺህ ሰዎች ይሳተፋሉ። የተሠበሠቡት መረጃዎችም በስምንት ዋና ዋና ጉዳዮች ተካተው ለውይይት ይፋ ተደርገዋል።

📋 የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ.ር) እንዳሉት እነዚህ አጀንዳዎች ሀገራዊ አንድነትን እና ሰላምን ማዕከል ያደረጉ ናቸው። በአጀንዳዎቹ በዋናነትም የሀገር ግንባታ፣ ዘላቂ ሰላም፣ የሃይማኖት እና የማንነት ጉዳዮች ይነሳሉ።

የሕግ የበላይነት፣ ሰብአዊ መብቶች እና የመሬት አያያዝም በስፋት ይዳሰሳሉ። የሕገ-መንግሥት ጉዳይ ደግሞ በተናጠል ከመታየት ይልቅ፣ በሁሉም አጀንዳዎች ውስጥ ተካቶ በየነጥቡ የሚነሳ ይኾናል ብለዋል።

ከእነዚህ ሀገራዊ ጉዳዮች ውጭ ያሉ የክልል እና የሴክተር ጥያቄዎችም በተለየ መልኩ ተለይተዋል። ምላሽ እንዲያገኙም ለሚመለከታቸው አካላት ይቀርባሉ ብለዋል።

🤝 የምክክሩ ውጤት ተአማኒ የሚኾነው ሂደቱ ግልጽ እና አካታች ሲኾን ብቻ ነው። ተጠያቂነት የሰፈነበት እና የሀገርን ጥቅም ያስቀደመ መኾንም አለበት። ለዚህም ሲባል ሂደቱ የሕዝቡን መንፈሳዊነት እና ባሕል ባከበረ መንገድ በሃይማኖት አባቶች፣ በሀገር ሽማግሌዎች እና በአባገዳዎች ምርቃት ሂደቱ መጀመሩን አስታውሰዋል። ይህም ከውጭ ርዕዮተ-ዓለሞች ነጻ የኾነ ሀገር በቀል ዕውቀትን መሠረት ያደረገ እንዲኾን አስችሎታል ነው ያሉት።

🤔 መጀመሪያ ላይ በሂደቱ ጥርጣሬ የነበራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ነበሩ። 🔍🤝 አሁን ግን የኮሚሽኑን ግልጽነት በተግባር አይተው አብረው ለመሥራት ወስነዋል ብለዋል። ይህም የሂደቱ ታማኝነት ማሳያ እንደኾነ አሳይተዋል።

ኢትዮጵያ ችግሮቿን በምክክር እየፈታች፤ ጠንካራ እና ሰላማዊት ሀገር ትኾናለች። ኢትዮጵያውያን ስለ ሀገራቸው፣ በሀገራቸው፣ ለሀገራቸው ይመካከራሉ፤ የጋራ መፍትሔም ይዘይዳሉ።

💡ሀገር በሰላም ንግግሮች እና በብሔራዊ ምክክር ትገነባለች።

አሚኮ_ዜና #EthiopianNationalDialogue

ዘጋቢ:- ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት በዓለም ከፍተኛ ተጓዦች ከተመረጡ የዩኔስኮ ምርጥ አምስት ቅርሶች መካከል ተካተቱ።