የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት በዓለም ከፍተኛ ተጓዦች ከተመረጡ የዩኔስኮ ምርጥ አምስት ቅርሶች መካከል ተካተቱ።

5

 

# ባሕር_ዳር: 23/2018 ዓ.ም የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት በዓለም ከፍተኛ ተጓዦች ከተመረጡ የዩኔስኮ ምርጥ አምስት ቅርሶች ተርታ ተሰልፈዋል።

በዓለም ላይ ያሉትን ሀገራት በሙሉ በመጎብኘት “UN Grandmaster” የተባለውን ታዋቂ የክብር ማዕረግ ያገኙ የዓለም ቁንጮ ተጓዦች፣ የሚመክሯቸውን ምርጥ የጉዞ መዳረሻዎች ይፋ አድርገዋል።

‘ዩሮኒውስ’ በተደረገ ጥናት እነዚህ ሁሉንም የዓለም ክፍሎች ያዩ አንጋፋ ተጓዦች ካስቀመጧቸው ተወዳጅ የዩኔስኮ የዓለም ቅርሶች መካከል የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በግንባር ቀደምትነት ከምርጥ አምስት ውስጥ መካተት ችሏል።

ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሰጠ ምስክርነት፣ ኢትዮጵያ አስደናቂ ታሪክ እና አስገራሚ ጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት መኾኗን በድጋሚ ያረጋገጠ መኾኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል። ተጓዦቹ እንደ አንኮር ዋት እና ታላቁ የቻይና ግንብ ካሉ ታዋቂ ቅርሶች ጎን ለጎን የላሊበላን ድንቅ የጥበብ ጥልቅነት እና መንፈሳዊ ግርማ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ይህም ለዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ሊታይ የሚገባው ቀዳሚ የጉዞ ዕንቁ መኾኑን ያሳያል።

መንግሥት ይህንን ዓለም አቀፍ ዕውቅና ይበልጥ ለማጎልበት የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ከማንኛውም ዓይነት የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ለመጠበቅ፣ ለመንከባከብ፣ ከዘላቂ የቅርስ ልማት እና ጥበቃ መርኾዎች ጋር በተጣጣመ መልኩ ለትውልድ ለማስተላለፍ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ የቅርስ ጥበቃ ሥራዎችን ከዘመናዊ የቱሪዝም መሠረተ ልማት ዝርጋታ ጋር በማቀናጀት፣ አካባቢው ለጎብኚዎች ምቹና ደኅንነቱ የተጠበቀ እንዲኾን በማድረግ የቱሪዝም ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚና ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሚያበረክተውን ሁለንተናዊ ጥቅም ለማሳደግ መንግሥት በትጋት እየተንቀሳቀሰ መኾኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!።

Previous article🌱 ኢትዮጵያ በ2050 የካርቦን ልቀትን ዜሮ ለማድረስ በቁርጠኝነት እየሠራች ነው! 🌍
Next article🇪🇹 በሀገራዊ ምክክር ከግጭት አዙሪት ወደ ዘላቂ ሰላምና የሀገር ግንባታ 🕊️🤝