ሰላምን ለማጽናት፣ የፍትሕ ሥርዓትን ለማጠናከር እና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል።

21
የአማራ ክልል ምክር ቤት ጉባኤውን እንደቀጠለ ነው። በጉባኤው የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የ2018 በጀት ዓመትን የአፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ የክልሉን ሰላም ለማጽናት፣ የፍትሕ አሥተዳደር ሥርዓትን ለማጠናከር፣ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል።
የወንጀል ምርመራ እና መዛግብትን በቅልጥፍና በመወሰን እየተሻሻለ መምጣቱንም ገልጸዋል። በ87 መዝገቦች በወንጀል የተመዘበረ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ማስመለስ መቻሉንም አንስተዋል። በተጨማሪም ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ካሬ ሜትር በላይ መሬት ወደ መንግሥት መመለሱን ተናግረዋል።
የ4 ሺህ 593 ሰዎች የመጀመሪያ ደረጃ የሀብት ምዝገባ እንዲከናወን ስለመደረጉም በሪፖርቱ ተመላክቷል። በማረሚያ ቤቶች ክትትል እና ድጋፍ በማድረግ ለበርካታ ታራሚዎች የሥነ ልቦና ግንባታ፣ ትምህርት እና ሥልጠና መሰጠቱንም ገልጸዋል።
የወንጀል ምርመራ አቅምን ለማሳደግ በተደረገው ጥረት፣ ምርመራ በማጣራት፣ በሙስና ወንጀል ምርመራ እና በፎረንሲክ ምርመራ ሥራዎች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቁመዋል።
በርካታ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማሠልጠን በሰላም ግንባታ ላይ ወደ ሥራ በማስገባት በሰላም ግንባታ እንዲሳተፉ ተደርጓል ነው ያሉት።
ለባለ ድርሻ አካላት ግንዛቤ በመፍጠር፣ ሥልጠናዎችን በመስጠት እና የሰላም ኮሚቴዎችን በማደራጀት ለሰላም ግንባታ እሴት ልዩ ትኩረት ተደርጎ መሠራቱንም ለምክር ቤቱ አብራርተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ስኬታማ ተግባራት ተከናውነዋል።