የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ስኬታማ ተግባራት ተከናውነዋል።

14
​የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሴቶች ክንፍ የ2018 ዓ.ም የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 ዓ.ም የእቅድ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ አካሂዷል።
​የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሴቶች ክንፍ ኀላፊ እሌኒ ዓባይ 2018 ዓ.ም «የማንሰራራት ዘመን» እንዲኾን የተገባው ቃል ዕውን መኾኑን እና የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።
📌 ከተመዘገቡ ዋና ዋና ስኬቶች መካከል የፖለቲካ ውክልና ዕድገት እንደሚጠቀስ ገልጸዋል። በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሴቶች ንቁ ተሳትፎ ምክንያት በምክር ቤቶች ያላቸው ውክልና በከፍተኛ ደረጃ አድጓል ነው ያሉት። በተወካዮች ምክር ቤት ያላቸው ተሳትፎ ከ40 በመቶ ወደ 47 በመቶ በላይ ማደጉን ነው የጠቀሱት። በክልል ምክር ቤት ደረጃም ከ36 በመቶ ወደ 43 በመቶ ከፍ ማለቱን አንስተዋል።
የበጎ ፈቃድ እና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሌላኛው ስኬት የተመዘገበበት ጉዳይ መኾኑንም አንስተዋል። የ5 ሚሊዮን ኮደርስ ንቅናቄን ጨምሮ በሰላም ግንባታ እና በማኅበራዊ አብሮነት ሥራዎች ከዕቅድ በላይ መፈጸም ተችሏልም ብለዋል። ባለፉት ስኬቶች ላይ በመመሥረትም ለቀጣይ በጀት ዓመት ለላቀ ውጤት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
​በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ባሕል ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ መስፍን አበጀ (ዶ.ር) የሴቶች ክንፍ አደረጃጀት ከክልል እስከ ቀበሌ እና ቤተሰብ ድረስ ተጽዕኖ ፈጣሪነቱ በተግባር እንደተረጋገጠ ገልጸዋል። ይህም የተመዘገቡ ታሪካዊ ድሎች እና ዕውቅና የሚገባቸው ስኬቶች መኾናቸውን አብራርተዋል።
📌 ቀጣዩ 2019 ዓ.ም “ጠንካራ አደረጃጀት ለላቀ ተጠቃሚነት “በሚል መሪ መልዕክት የሚመራ እንደሚኾንም አመላክተዋል። በእናቶች እና በሴቶች የሰላም ግንባር አደረጃጀት አማካኝነት በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ በትኩረት የሚሠራ መኾኑንም አስገንዝበዋል።
ይፋ በተደረገው የ2019 የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ800 ሺህ በላይ የሴቶች ክንፍ አባላት በመሳተፍ ሚሊዮኖችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ እንደኾነም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleበክልሉ ለ173 ሺህ ባለይዞታዎች የሁለተኛ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ተሰጥቷል።
Next articleሰላምን ለማጽናት፣ የፍትሕ ሥርዓትን ለማጠናከር እና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል።