
ባሕር_ዳር: 23/2018 ዓ.ም ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቷ የታደለች ሀገር ናት። ነገር ግን ሀብቱ በአግባቡ ሳይለማ እና ሳትጠቀምበት እንደቆየች መረጃዎች ዋቢ ናቸው።
ይህንን ለመቀልበስ እና የተፈጥሮ ሀብትን ለማስጠበቅ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሀሳብ አምጪነት እና አነሳሽነት 2011 ዓ.ም ላይ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ተጀምሯል። መርሐ ግብሩ ከተጀመረ ወዲህ በርካታ ለውጦች እየተመዘገቡ መኾናቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።
በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ እና አጠቃቀም መሪ ሥራ አሥፈጻሚ እና በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ደግሞ የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ አሥተባባሪ ፀሐፊ ፋኖሴ መኮንን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከተጀመረ ወዲህ ባለፉት ዓመታት ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞችን መትከል ተችሏል ብለዋል።
በዚህም ለውጦች ተመዝግበዋል ነው ያሉት። የተጀመረው “የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር” የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል በሚደረገው ጥረት ታላቅ የለውጥ ምዕራፍ ኾኗልም ብለዋል።
ከተገኙ ለውጦች መካከል፦
✅ የደን ሽፋን ማደግ፦ ከነበረበት 17 ነጥብ 2% ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ብሏል።
✅ የአፈር መሸርሸር በመቀነስ ወደ ወንዞች ይገባ የነበረው ደለል ቀንሷል፤ ይህም የአፈርን ለምነት ታድጓል ብለዋል።
✅ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ ድል ተፈጥሮ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ አድርጓል።
✅ በተፋሰስ ልማት አማካኝነት የፍራፍሬ ልማት፣ የንብ ማነብ እና የከብት እርባታ ተጠናክሮ ገቢን በማሳደግ የኑሮ ደረጃን ማሻሻል ተችሏል፤
✅ምርት እና ምርታማነት በማሳደግ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማግኘት ተችሏል ነው ያሉት።
✅ ማኅበረሰቡ ባለቤት ኾኖ 197 ሺህ 843 የማበረሰብ ተፋሰሶች በዘላቂነት እያለማ ይገኛል።
ለዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብርም የተለያዩ ዝግጅቶች መደረጋቸውን አንስተዋል።
በተለይም በበልግ አብቃይ አካባቢዎች እስካሁን ከ1 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል ብለዋል። 8 ነጥብ 8 ቢሊዮን ችግኞች ተዘጋጅተው፣ 6 ነጥብ 8 ቢሊዮን ጉድጓዶች ተቆፍረዋል ነው ያሉት።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የሀገሪቱን ገጽታ በመቀየር እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ላይ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነውም ብለዋል። መርሐ ግብሩ በስኬት እየተከናወነ በመኾኑ ኢትዮጵያን ለዓለም ገለጦ ያሳዬ ትልቅ የስኬት ምዕራፍ መኾኑን አስረድተዋል።
#አረንጓዴ_አሻራ #የችግኝ_ተከላ #GreenLegacy #EthiopianGreenLegacy
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
