
ፍኖተ ሰላም: ሰኔ 23/2018 ዓ.ም በምዕራብ ጎጃም ዞን
”ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ መልዕክት ዞናዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በቡሬ ዙሪያ ወረዳ ዋድራ ቀበሌ ተካሂዷል።
የቡሬ ዙሪያ ወረዳ ምክትል አሥተዳዳሪ ተሻገር አያና በወረዳው የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ከጀመረ ወዲህ በርካታ ለውጦች መመዝገባቸውን አንስተዋል።
በተለይ ቡና እና ፍራፍሬ ችግኞችን በመትከል አርሶአደሮች በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ኾነዋል ብለዋል።
በዚህ ዓመት ከ6ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የተለያየ ፋይዳ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ አጉማሴ አንተነህ በዞኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር መካሄድ ከጀመረ በኋላ የአርሶአደሮች የችግኝ የመትከል ባሕል በእጅጉ አያደገ መምጣቱን አንስተዋል።
የተተከሉ ችግኞች ተራቁተው የነበሩ መሬቶችን እንዲያገግሙ እና ተፋሰሶችን ለማልማት ሰፊ ድርሻ መወጣታቸውንም ነው ያስረዱት።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብርም ከ134 ሚሊዮን የሚልቁ የደን፣ የቡና እና ፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል እየተሠራም ነው ብለዋል።
በዚህ ዓመት ለቡና እና ፍራፍሬ ችግኞች ልዩ ትኩረት መሰጠቱንም ጠቁመዋል። በአምስት ወረዳዎች ላይ ቡና እና አቮካዶን በኩታ ገጠም ለመትከል ከሁለት ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተዘጋጅተዋል።
አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡ ተሳታፊዎች ባለፉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች በተለያየ መንገድ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መኾኑን ተናግረዋል።
በዚህ ዓመትም የደን፣ የቡና እና የፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል በንቃት እንደሚሳተፉ ነው የጠቆሙት። ችግኞችን ከመትከል ባሻገር የሚፈለገውን ጠቀሜታ እንዲሰጡ ሁሉም እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባውም አሳስበዋል።
#አሚኮ_ዜና #ምዕራብ_ጎጃም_አረንጓዴ ልማት #GreenLegacyEthiopia 🇪🇹
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!።
