
ባሕር ዳር: ሰኔ 23/2018 ዓ.ም የአማራ ክልል ሚሊሻ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ሦሥት አሥርት ዓመታት የክልሉን፣ የኢትዮጵያን ሰላም፣ ሉዓላዊነት እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በማስከበር ሂደት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ከማኅበረሰቡ አብራክ የወጣው እና በቅርቡ መዋቅሩ ተሻሽሎ በኮሚሽን ደረጃ የተደራጀው ይህ ኀይል በሰላም ጊዜ የልማት አርበኛ፣ በችግር ጊዜ ደግሞ የሕግ መከታ በመኾን እያገለገለ ይገኛል።
የአማራ ክልል ሚሊሻ ኮሚሽን ኮሚሽነር አስቻለ አላምሬ ተቋሙ በኮሚሽን ደረጃ መደራጀቱ የወሳኝነት ሚናው ከፍ እንዲል አስችሎታል ብለዋል። አደረጃጀቱን ከሻለቃ ወደ ክፍለጦር እንዲያሳድግ፤ ቀጥተኛ ትዕዛዝን በመተግበር የሕግ ማስከበር ሚናውን እንዲያጎለብት ዕድል ፈጥሮለታል ነው ያሉት።
ያጋጠመውን የክልሉን የሰላም ችግር በመፍታት ሰላምን ለማረጋገጥ የክልሉ ሚሊሻ ኮሚሽን ከክልሉ መንግሥት ጋር በመነጋገር ራሱን የቻለ የሰላም አስከባሪ አደረጃጀት መፈጠሩንም ተናግረዋል። ሰላም አስከባሪ ኀይሉ በሚሊሻ ኮሚሽኑ ውስጥ የኾነ፤ የተሻለ ወታደራዊ ብቃት ያላቸው ወጣቶች የተደራጁበት መኾኑን ገልጸዋል። ይህ ኀይል የክልሉን ሰላም እና መረጋጋት ለማምጣት ትልቅ አቅም ኾኖ እየሠራ፣ መስዋዕትነት እየከፈለ እና ጠላትን እየደመሰሰ መኾኑንም ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ትልቅ የሚሊሻ ኀይል ገንብቷልም ብለዋል። ከሌሎች የጸጥታ ተቋማት ጋር በማቀናጀት የክልሉን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ትልቅ ወታደራዊ አቅም ኾኖ እያገለገለ እንዳለም አንስተዋል። በጽንፈኛ ኀይሉ ተይዘው የነበሩ አካባቢዎችን በማስለቀቅ ሂደት እንደ ሌሎች የጸጥታ ኀይሎች ኹሉ የሚሊሻ ኀይሉ ድርሻም ከፍተኛ መኾኑን ጠቅሰዋል።
የሕዝቡን ሰላም ወደነበረበት ለመመለስ በተደረገው ተጋድሎ የክልሉ የሚሊሻ ኀይል መስዋዕትነት መክፈሉን ተናግረዋል። አሁን ያለው አንጻራዊ ሰላም እንዲመጣም የሚሊሻ ኀይሉ ዋጋ ከፍሏል። ወደፊትም ዘላቂ ሰላም እስከሚረጋገጥ ጠንክሮ እንደሚሠራ ነው የተናገሩት።
የክልሉ ሚሊሻ ኮሚሽን 30ኛ ዓመት በዓሉን ሲያከብር ያለፉትን የ30 ዓመታት ታሪክ ከመዘከር ባለፈ ጀብድ የፈጸሙ ጀግኖች መሸለማቸውን፤ ለክልሉ ሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት ሲሉ ጀብድ ፈጽመው መስዋዕትነት ለከፈሉ አባላት ቤተሰቦች ድጎማ እና የክብር ሽልማት መስጠታቸውንም ተናግረዋል።
የሚሊሻ ኀይሉ እንደ ክልል ያጋጠመውን የጸጥታ ችግር ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍ ያለውን ሚና በመገንዘብ የክልሉ መንግሥት የካሳ እና የድጎማ መመሪያ አውጥቶ እየደገፈው መኾኑን ተናግረዋል።
ከኹሉም በላይ ደግሞ ሚሊሻ እና ሕዝብ የተቆራኙ በመኾናቸው ሕዝቡ ድጋፉን ማጠናከር አለበት ብለዋል። ሚሊሻ ጠንክሮ ሲሠራ የሕዝቡን ሰላም እና ደኅንነት ያስጠብቃል፥ ሰላም እና ደኅንነቱ የተጠበቀለት ሕዝብ ደግሞ ሚሊሻውን መደገፍ አለበት ነው ያሉት።
ቤተሰቦቻቸውን መደገፍ፣ ልጆቹን ማስተማር፣ እርሻቸውን ማረስ ይጠይቃልም ብለዋል። የክልሉ ሕዝብ ጠንካራ ድጋፍ እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል። አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት።
#አሚኮ_ዜና #Milisha💪 #PeaceAmhara #PeaceEthiopia 🕊️🇪🇹
ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!።
