በዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሁነቶች ተመዝግበዋል።

2

 

የአማራ ክልል ሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት የአገልግሎት አሰጣጡን ዘመናዊ እና ቀልጣፋ በማድረግ ጥራት ያለው መረጃ ለመሰነድ አልሞ እየሠራ ይገኛል። ይህን እያከናወነ ያለውን ተግባር በተመለከተም መግለጫ ሰጥቷል።

​መግለጫውን የሰጡት የአማራ ክልል ሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት ኅላፊ መዓዛ በዛብህ ተቋሙ ከስም ለውጥ ባሻገር የምዝገባ ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ በማዘመን እና መዋቅሩን እስከ ታችኛው እርከን በማውረድ ተደራሽነቱን እያሰፋ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

​በ2018 በጀት ዓመት ከ982 ሺህ በላይ ሁነቶችን ለመመዝገብ ታቅዶ ከ1ሚሊዮን በላይ ሁነቶች ተመዝግበዋል ብለዋል። ይህም የዕቅዱን 107 በመቶ ማሳካት እንደቻሉ ነው ያመላከቱት።

በክልሉ በሚገኙ ከ4ሺህ በላይ የምዝገባ ጣቢያዎች አማካኝነት የዜጎችን እንግልት በመቀነስ ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል።

​በተለይም በጤና ተቋማት አማካኝነት በሚሰጠው “የአንድ ማዕከል አገልግሎት” ከ136 ሺህ በላይ የልደት እና የሞት ሁነቶች ተመዝግበዋል ነው ያሉት።

ይህም ዜጎች አገልግሎቱን በቀላሉ እንዲያገኙ ያስቻለ መኾኑን ነው የገለጹት። ጥራት ያለው መረጃ ለማረጋገጥ እና ሀሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከል ጠንካራ ጥረትም ተደርጓል።

በተለይም ለክብር መዝገብ እና ለሌሎች ይወጣ የነበረውን ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ማዳን ተችሏል ነው ያሉት። አሠራሩን በማዘመን ባለጉዳዮች ሳይጉላሉ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።

ሥራዎች ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት በመሠራቱ ውጤቶች ተመዝግበዋል ነው ያሉት። ​ የምዝገባ አገልግሎቱን በአግባቡ መጠቀም ለዜጎች መብት እና ለሀገር ደኅንነት ወሳኝ መኾኑንም አስገንዝበዋል።

ተቋሙ በቀጣይም ሁሉንም የምዝገባ ሥርዓቶች በቴክኖሎጂ በማስተሳሰር፣ ብቁ እና ጥራት ያለው መረጃ በመገንባት ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚሠራ ተመላክቷል።

#አሚኮ_ዜና #የአማራClivilStatus

ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!።

Previous articleየአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል።