የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል።

3

 

የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን 10ኛውን መደበኛ ጉባኤ በባሕርዳር አካሂዷል።

የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፍሬሰላም ዘገየ ጉባኤው ለአካል ጉዳተኞች ድምጽ የመኾን፣ በመንግሥት እና በአካል ጉዳተኞች መካከል ድልድይ በመኾን የወጡ ሕጎች እና አዋጆች በተግባር እንዲተረጎሙ የማድረግ ዓላማ እንዳለው ተናግረዋል። ከዚህ ባሻገር በአካታችነት እና ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረቱ ሥራዎች እንዲሠሩ ለማድረግ ነው ብለዋል።

በክልሉ የሚገኙ 98 በመቶ የሚኾኑ አካል ጉዳተኞች ዛሬም ድረስ በኢኮኖሚያዊ፣ በማኅበራዊ እና በፖለቲካዊ ችግሮች ውስጥ እንደሚገኙ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ ባለፉት ጊዜያት ከመንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር አካል ጉዳተኞች ተጠቃሚ የሚኾኑባቸው ሥራዎችን ሲሠሩ መቆየታቸው ገልጸዋል።

በዋናነት የአካል ጉዳተኞችን የተጠናከረ መረጃ የመያዝ፣ መስማት የተሳናቸው ቋንቋ (የምልክት ቋንቋ) የሥራ ቋንቋ እንዲኾን ጥያቄ ማቅረብ፣ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የአካል ጉዳተኞች ጥያቄ ትኩረት እንዲያገኝ ሀሳብ ማቅረብ እና ለአካል ጉዳት ምክንያት የኾነው ጦርነት (ግጭት) እንዲቆም እንደ ባለድርሻ አካል ጥረት ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

በዛሬው ጉባኤ የአገልግሎት ዘመናቸውን የጨረሱ መሪዎችን መተካት እና የመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ ተደርጓል ብለዋል። ለቀጣይም የመረጃ ሥርዓት፣ ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ እና ማገገሚያ፣ አካታችነት እና ውክልና ላይ በትኩረት ለመሥራት አቅጣጫ መቀመጡንም ገልጸዋል።

በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ንፁሕ ሽፈራው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባለው ውሥብሥብ ችግር (በተለይም በግጭቶች) ምክንያት የአካል ጉዳተኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን እና በርካታ አካል ጉዳተኞች መኖራቸውን ተናግረዋል።

ጉባኤው ጠንካራ፣ በቴክኖሎጂ የዳበረ፣ ከመንግሥት ጥገኝነት የተላቀቀ እና ራሱን የቻለ አደረጃጀት በመፍጠር ቤት ውስጥ ቁጭ ብለው አስታዋሽ ላጡ እና ወደ አደባባይ ለመውጣት አጋዥ ለሌላቸው ወገኖች ድምጽ መኾን እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

በክልሉ ውስጥ የአካል ጉዳተኞችን ቁጥር ለይቶ የማወቅ፣ ያሉበትን ሁኔታ የመለየት፣ በማኅበር እንዲደራጁ የማድረግ እና ሊፈቱላቸው የሚገቡ ችግሮችን የመለየት ሥራ ትኩረት እንዲደረግበትም አሳስበዋል።

የጉባኤው ተሳታፊዎችም በክልሉ በሚገኙ ሁሉም አካባቢዎች አካል ጉዳተኞች በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ተጠቃሚ እና ተሳታፊ እንዲኾኑ የሚያስችሉ ሥራዎችን ከዚህ በፊት ከነበረው በተሻለ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

💬 በእርስዎ አካባቢ የአካል ጉዳተኞች አካታችነት ተግባር እንዴት ይገለጻል? ሀሳብዎን በኮሜንት ያካፍሉን?

#አሚኮ_ዜና #Amhara #Inclusion #DisabilityRights #Ethiopia #SocialJustice

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየኮሞቦልቻ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ዓለማቀፍ ዕውቅና አገኘ።
Next articleበዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሁነቶች ተመዝግበዋል።