
የአማራ ክልል ምክር ቤት 12ኛ መደበኛ ጉባኤውን ከሐምሌ 23/2018 ዓ.ም ጀምሮ ያካሄዳል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ መደበኛ ሥብሠባውን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል። ዋና አፈ ጉባኤዋ በመግለጫቸው ምክር ቤቱ ከሐምሌ 23/2018 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 26/2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ እና ጉባኤው የምክር ቤቱን የ5 ዓመታት አጠቃላይ የሥራ አፈፃፀም የሚገመግም መኾኑን ነው የገለጹት።
በጉባኤው 6ኛው ዙር ባለፉት 5 ዓመታት የተከናወኑ አጠቃላይ ሥራዎች ተገምግመው በምክር ቤቱ ይጸድቃሉ ብለዋል። የ2018 ዓ.ም የአሥፈፃሚ አካላት ዕቅድ ክንውን፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የዋና ኦዲተር የዕቅድ አፈፃፀሞች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ነው ያሉት።
በጉባኤው በ2018 ዓ.ም ጥቅም ላይ የዋለ ተጨማሪ በጀት ቀርቦ ከተመረመረ በኋላ ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅሰዋል።
እንዲሁም የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ እና ለምክር ቤቱ ሥራዎች የሚውል በጀት ላይ ውይይት እንደሚደረግ ነው በመግለጫው ያብራሩት።
የክልሉ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን በተመለከተም ውይይት ይደረጋል ነው ያሉት።
በተለይም በክልሉ እየመጡ ያሉ የልማት ውጤቶች፣ ከኅብረተሰቡ የሚጠበቁ ተሳትፎዎች እና የወደፊት የልማት ሥራዎችን በተመለከተም ሰፊ ውይይት ይካሄዳል ብለዋል።
የምክር ቤቱ 6ኛ ዙር ጥቅል ሪፖርትን ጨምሮ ሌሎች ልዩ ልዩ አጀንጃዎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ነው ያሉት በመግለጫቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
