
ባሕር ዳር: ሰኔ 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው የኢትዮጵያ የደን ሽፋን በ1990ዎቹ ከነበረበት 40 በመቶ በጊዜ ሂደት ወደ ሦሥት በመቶ ወርዶ ነበር።
ለዚህ የደን መመናመን ዋነኛ ምክንያቶች የደን ጭፍጨፋ እና ዘላቂነት የሌለው የመሬት አጠቃቀም ናቸው። ደካማ የሀብት አሥተዳደር እና ከልክ ያለፈ ግጦሽ ለችግሩ መባባስ ተጨማሪ ምክንያቶች ኾነው ይነሳሉ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀው ከ2000 እስከ 2013 እ.ኤ.አ በኢትዮጵያ በየዓመቱ በአማካይ 72 ሺህ ሄክታር በደን የተሸፈነ መሬት ይመነጠራል። ይህ የመሬት መራቆት የግብርና ምርታማነትን በማዳከም እና የውኃማ አካላትን በመቀነስ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። በዚህም ምክንያት ሀገሪቱ በየዓመቱ በአማካይ የ4 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ሲያደርስ መቆየቱን የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የመረጃ መረብ በኾነው ‘ReliefWeb’ እ.ኤ.አ. በ2025 የወጣ ጥናት አረጋግጧል። የብዝኀ ሕይወት መጥፋት፣ ድርቅ፣ ጎርፍ እና የምግብ ዋስትና እጦት ተጨማሪ ፈተናዎቹ ናቸው።
መንግሥት እነዚህን አንገብጋቢ የተፈጥሮ መራቆት ተግዳሮቶች ያገናዘበ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃን፣ ዘላቂ አሥተዳደርን እና አረንጓዴ ኢኮኖሚን የልማት አጀንዳው ማዕከል አድርጓል። በ2011 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብርን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አነሳሽነት ይፋ ተደረገ።
የዚህ ግዙፍ ብሔራዊ ንቅናቄ አንዱ ዓላማ የተራቆተውን እና የተጋጋጠውን ሥነ-ምህዳር መልሶ ማልማት፣ የደን ጭፍጨፋን በዘላቂነት መከላከል፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ የአየር ንብረት ሚዛንን ምቹነት መጠበቅ ነው። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሥራ ዕድሎችን የመፍጠር ትልቅ ግብም አንግቦ ነው የተጀመረው።
መንግሥት ለአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ስኬት ከዓመታዊ በጀቱ ጭምርም ይመድባል።
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን በማስተባበር ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ የተተገበረው ይህ መርሐግብር ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ፋይዳ ያላቸው በርካታ ስኬቶች ተመዝግበውበታል።
👉 እስካሁን ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።
👉 በሐምሌ 2017 ዓ.ም በአንድ ጀምበር ከ714 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን ተመዝግቧል።
👉 የሀገሪቱ ዓመታዊ የደን ጭፍጨፋ መጠንም ወደ 27 ሺህ 703 ሄክታር ዝቅ ማለቱን ጥናት አረጋግጧል።
👉 የሀገሪቱ አሁናዊ የደን ሽፋንም ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ማለት ችሏል።
👉 ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሁለተኛዋ የአቮካዶ ላኪ ሀገር የኾነችውም የአረንጓዴ አሻራን መሰረት አድርጎ በተሠራ ሥራ ነው።
👉 በችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች፣ በደን ግብርና እና በዘላቂ መሬት አያያዝ ዘርፎች ከ767 ሺህ በላይ የሥራ ዕድሎች መፍጠሩንም ጥናቱ ጠቁሟል።
👉 በየዓመቱ ይሸረሸር የነበረው የአፈር መጠን በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ ወደ ወንዞች እና ግድቦች የሚገባው የደለል መጠን ከ2 ቢሊዮን ቶን ወደ 208 ሚሊዮን ቶን ዝቅ እንዳለም ጥናቶች ያመለክታሉ።
👉 ይህ የተፈጥሮ ማሻሻያ እ.ኤ.አ. እስከ 2030 ድረስ 297 ሚሊዮን ቶን የካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀትን ለማስወገድ የሚያስችል ነው።
የሙቀት መጨመር ተገቢው የአረንጓዴ ልማት ሥራ ካልተሠራ ከዛሬ 74 ዓመት በኋላ እስከ 97 በመቶ ምቹ መኖሪያ አካባቢዎችን ሊያጠፋ እንደሚችል በቻይና የተሠራ ጥናት ያመለክታል።
በመኾኑም የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሐግብር የአየር ንብረት ስጋቶችን ለመቋቋም እና የተፈጥሮ ሚዛንን ለመጠበቅ የሚያስችል ዓይነተኛ እና ተግባራዊ የመፍትሔ ሞዴል ነው።
#አረንጓዴአሻራ #ኢትዮጵያ #የተፈጥሮጥበቃ #የአየርንብረትለውጥ #የደንልማት #GreenLegacy #Ethiopia #ClimateAction #Sustainability
ዘጋቢ ፦ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
