ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በምሥራቅ አፍሪካ የመጀመሪያውን የእንስሳት ሆስፒታል አስመረቀ 🏆🏥

6

 

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸውን የተለያዩ ፕሮጀክቶች አስመርቋል።

በዩኒቨርሲቲው የተመረቁ ፕሮጀክቶች ለትምህርት ጥራት እና እድገት ወሳኝነት አላቸው ያሉት በትምህርት ሚኒስቴር የአሥተዳደር መሠረተ ልማት ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ሰለሞን አብርሃ (ዶ.ር) ተማሪዎች በትግበራ የሚማሩባቸው ናቸው ብለዋል።

የመረጃ እና ቴክኖሎጂ ግንኙነት ቋት የተማሪዎችን መረጃ በአግባቡ ለመሰነድ እና ከወረቀት ንክኪ በማላቀቅ ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መኾኑንም ተናግረዋል። መረጃዎች በሳይበር ደኅንነት ቴክኖሎጂ ተጠብቀው እንዲቀመጡ ያግዛል ነው ያሉት።

የእንስሳት ሕክምና ሆስፒታሉ በትምህርት እና በምርምር ለሀገር የልህቀት አካዳሚ ኾኖ እንደሚያገለግልም ገልጸዋል። በሀገር ግንባር ቀደም ሆስፒታል መኾኑንም አንስተዋል።

የጎንደር ዩንቨርስቲ ፕሬዝዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ.ር)
ዩኒቨርሲቲው ባለፈው የትምህርት ዘመን 22 ፕሮጀክቶችን ማስመረቁን አስታውሰዋል። ዛሬ ደግሞ የእንስሳት ሕክምና ማስተማሪያ ሆስፒታል፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳ፣ የመምህራን የጋራ መኖሪያ ሕንጻዎች እና የመረጃ እና ግንኙነት ቋት ማስመረቃቸውን ገልጸዋል።

የእንስሳት ሆስፒታሉ በሀገር እና በክልሉ ያለውን እምቅ የእንስሳት ሀብት የጤና ዋስትና የሚያረጋግጥ መኾኑንም አንስተዋል።

ተማሪዎች በትምህርታቸው ውጤታማ መኾን የሚችሉት በአዕምሮ ብቻ ሳይኾን በአካልም ጠንካራ ሲኾኑ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ በዩኒቨርሲቲው የተገነባው የስፖርት ማዘውተሪያ ለዚሁ የሚረዳ ነው ብለዋል።

የመረጃ እና ቴክኖሎጂ ግንኙነት ቋት ተማሪዎች የፈጠራ አዳዲስ ዲጂታል መተግበሪያዎችን እንዲያመርቱ ምቹ ምህዳርን የሚፈጥር መኾኑን ገልጸዋል።

የእንስሳትን ጤንነት በተሻለ ሁኔታ ለመጠበቅ የሆስፒታሉ ግንባታ ወሳኝ ነው ያሉት ደግሞ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ሕክምና እና እንስሳት ሳይንስ ኮሌጅ ዲን አቸነፍ መላኩ (ዶ.ር) ናቸው። በምሥራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ የእንስሳት ሆስፒታል መኾኑንም አንስተዋል።

ሆስፒታሉ ዘመናዊ የማማከር እና የምርምር ክፍሎች፣ የቀዶ ጥገና ክፍሎች፣ የበሽታ መመርመሪያ ላበራቶሪዎች እና የምርምር ድጋፍ መስጫ ክፍሎችን የያዘ መኾኑንም አስረድተዋል።

UniversityOfGondar #VeterinaryHospital #ጎንደር_ዩኒቨርሲቲ #የእንስሳት_ሆስፒታል

ዘጋቢ:- አምሳሉ አደራጀው

Previous article🇪🇹 ኢትዮጵያ በምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር የአፍሪካ የልህቀት ማዕከል ለመኾን እየሠራች ነው 💊