
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ በኢትዮጵያ የቻይና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ቼን ሀይን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ በማሸነፉ ከቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የተላከውን የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክትም ተቀብለዋል፡፡
ፓርቲው በላከው የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት በብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት እና የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) መሪነት፣ በመደመር እሳቤ በኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው ሰላምና መረጋጋት፣ ብሔራዊ አንድነት እና ሁለንተናዊ ብልጽግና እየተረጋጋጠ እንደሚሄድ ያለውን እምነት ገልጿል፡፡
የምርጫው ውጤትም የኢትዮጵያ ሕዝብ ለብልጽግና ፓርቲ ያለውን ልባዊ ድጋፍ የሚያሳይ እና በቀጣይም ብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያን ሕዝብ አስተባብሮ በመምራት ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር የማሻገር ግብን እውን እንደሚያደርግ ፓርቲው እንደሚያምን ጠቅሷል፡፡
በቀጣይም የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ከዚህ ቀደም በሁለቱ ፓርቲ ፕሬዝዳንቶች አማካይነት የተደረሱ ስምምነቶች ተግባራዊ እንዲደረጉ በትኩረት መሥራቱን እንደሚቀጥል አስታውቋል።
በልምድ ልውውጥ እርስ በእርስ በመማማር ሂደት መንግሥታዊ ልምዶችን በመለዋወጥ ለኢትዮጵያ እና ቻይና እድገት አበክሮ በመሥራት በየትኛውም ሁኔታ የማይናወጥ አጋርነትን እየገነባ እንደሚሄድ ገልጿል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ብልጽግና ፓርቲ በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል ያለው የፓርቲ ለፓርቲ፤ የመንግሥት ለመንግሥት እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡
የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ እና ብልጽግና ፓርቲ ሀገር በቀል በኾኑ እሳቤዎች እየተመሩ ሀገር በቀል መፍትሔዎችን በማፍለቅ ውጤት ማስመዝገብ መቻላቸውን ገልጸዋል። ዘርፈ ብዙ በኾኑ ጉዳዮች ተባብሮ ከመሥራትም ባሻገር በተለያየ መስክ እየተደረገ ላለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ያላቸዉን ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ሚስተር ቼን ሀይ በብልጽግና ፓርቲ መሪነት በመደመር እሳቤ በኢትዮጵያ እየተመዘገቡ ላሉ ድሎች ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራትም በርካታ አዳዲስ የቻይና ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል። በማዕድን፤ በአገልግሎት፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ በኮንስትራክሽን እና በዓለምአቀፍ ግንኙነት በጋራ በመሥራት ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
ከብልጽግና ፓርቲ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው
በቀጣይም በሁሉም መስኮች የተገኙ ድሎችን ለማስቀጠል እና በጋራ ለመሥራት በብልጽግና ፓርቲ እና በቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ መካከል ያለው ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
