
አዲስ አበባ: ሰኔ 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ለመረጠው ሕዝብ የምሥጋና መርሐግብር በዓድዋ ድል መታሰቢያ አከናውኗል።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞገስ ባልቻ በ2018 ጠቅላላ ምርጫ ከተፎካከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብልጽግናን ስለመረጣችሁን እናመሠግናለን ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ
በምርጫው ያሸነፈው ብልጽግና ፓርቲ ብቻ ሳይኾን ኢትዮጵያ ናት ነው ያሉት።
ሁሉም ተሟልቶላችሁ፣ እርካታ ተሰምቷችሁ እና ሁሉም ጥያቄዎች ተመልሰው ሳይኾን በፈጸምናቸው ሥራዎች አምናችሁ፣ የጎደለውን ይሞላሉ፣ የጀመሩትን ይጨርሳሉ ብላችሁ ተስፋ ስለጣላችሁብን እና ተጨማሪ የሥልጣን ጊዜ እንደሰጣችሁን እንገነዘባለን ብለዋል።
ምርጫው እንዳይሳካ የነበሩ የሚዲያ ዘመቻዎች እና ማስፈራሪያዎችን በጽናት አልፋችሁ፣ ከሌሊት እስከ ሌሊት ሳትሰለቹ ለመረጣችሁ ሁሉ ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ አድርጋችኋልና ምሥጋና ይገባችኋል ነው ያሉት።
የሰጣችሁን ተጨማሪ ጊዜ ያጎደልናቸውን እንድናሟላ፣ ያላሳካናቸውን እንድናሳካ፣ ያላደረስነውን ልማት እንድናዳርስ ቃል ኪዳናችንን የምናድስበት ነው ብለዋል።
ምርጫውን ጨረስን ማለት ለምርጫ ያስቀመጥናቸውን ግቦች አሳካን ማለት እንጂ ሥራችንን አጠናቀቅን ማለት አይደለም ነው ያሉት።
ሁሉንም ያሳካነው ከሕዝቡ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን በመሥራታችን ነው ያሉት ከንቲባዋ አሁንም ኢትዮጵያን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ፣ ለልጆቻችን ዕዳ ሳይኾን ዘላቂ ሰላም ያለባት ውብ፣ ጽዱ እና ለኑሮ የምትመች ሀገር ለማስረከብ በቅንነት፣ በታማኝነት እና ሙሉ ጊዜን በትጋት ለመሥራት ቃል አንገባለን ብለዋል።
የቀድሞው ገጽታው ተቀይሮ በጀልባ ለመዝናናት ምቹ ተደርጎ የለማውን የእንጦጦ ቀበና የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክትን ሁሉም እንዲጎበኝ ጥሪ አቅርበዋል።
#አሚኮ_ዜና #የአዲስ_አበባ #ብልጽግና_ፓርቲ_ምሥጋና #ኢትዮጵያ
ዘጋቢ፦ ድልነሳ መንግሥቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
