✨ “ትውልድ የሚቀባበለው የሰላም ችቦ፤ ከባሕላዊ የግጭት አፈታት እስከ ሀገራዊ ምክክር”

5

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰው ዘር መገኛ፤ በቋንቋ በሃይማኖት፣ በባሕል እና ወግ እንደ ነብር ዥንጉርጉር፤ በልዩነት ውስጥ አንድነትን በአለት ላይ የገነባች፤ ከማንም በፊት ሀገረ መንግሥትን ለዓለም ያስተዋወቀች፤ በቅዱሳት መጻሕፍት በተደጋጋሚ የተጠቀሰች ጥንታዊት፤ የሃይማኖተኞች ሀገር፤ የአፍሪካ እናት፤ የማይሰበር እና የማይጋሩት ክብረ ወሰን ባለቤት ኢትዮጵያ አሁንም በዚሁ ማማ ላይ ናት።

መሠረቷ በጀግንነት እና በነጻነት ላይ የቆመ፤ በትዕግስት እና ይቅር ባይነት ድልድይ ጸንቶ ለትውልድ የሚሻገር ነው። ነፋስ ቢመታው፤ ጎርፍ ቢገፋው እንኳን አይናወጥም። የሰላም እና የይቅርታ መሻቷ ከራሷ ያለፈ፤ ለጎረቤቶቿ የተረፈ መኾኑ ደግሞ ዛሬም ድረስ የሌላኛው ከፍታዋ ሕያው ማሳያ ነው።

ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያ ግጭት፣ አለመግባባት፣ ጦርነት እና መሰል አስከፊ መልኮች የሏትም ማለት አይደለም። ይህ ለኢትዮጵያ ባይገባትም ከትናንት እስከ ዛሬ የተጣቧት የታሪኳ አካል ናቸው።

ኢትዮጵያውያን ገና እንደ ማኅበረሰብ ሲኖሩ፣ እንደ ሀገር ሲሰባሰቡ ግጭት እና አለመግባባት ተፈጥሯዊ መኾኑን ቀድመው ተገንዝበዋል። ነገር ግን ችገሮቻቸውን በሀገር በቀል በባሕላዊ የግጭት መፍቻ ሥርዓቶች እየፈቱ ሰላምን ሲያጸኑ ኖረዋል።

እነዚህ ሥርዓቶች የተኳረፉትን በማቀራረብ፤ የተጣሉትን በማስታረቅ፤ የተጋደሉትን ደም በማድረቅ ሰላም እንዲሰፍን እና ኢትዮጵያውያን በአንድነት እንዲቀጥሉ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።

ኢትዮጵያውያንን ለግጭት የሚጋብዝ አንዳች ምድራዊ መንስኤ ባይኖራቸውም ከግጭት አዙሪት አሁንም አልተላቀቁም። ሥልጣኔዋን፣ እድገቷን እና ብልጽግናዋን የሚፈሩ የውጭ ጠላቶቿ ደግሞ መንስኤ ናቸው።

ኢትዮጵያ ሰላሟን ለማጽናት፤ ለእድገቷን ለማረጋገጥ መፍትሔ እየዘየደች ቀጥላለች። ለዚህም አለመግባባቶችን በጠረንጴዛ ዙሪያ በውይይት እና በምክክር በመፍታት እድገቷን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሠራች ትገኛለች።

ግጭቶችን እና አለመግባባቶችን ለመፍታት ታዲያ ማስታገሻ ሳይኾን ከባሕላዊ ሥርዓቶች የተቀዳ ነገር ግን አካታች እና ዘላቂ መፍትሔን የሚያመጣ ፈውስ ነው የሻተችው። እሱም ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርዓያ እንደገለጹት የምክክር ኮሚሽኑ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፤ ከምሁራን እና ከሌሎች የተቀዱ ሀገር በቀል ዕውቀቶች ለምክክር ኮሚሽኑ ቅድመ ዝግጅት ግብዓት ኾነው ማገልገላቸውን ጠቅሰዋል።

የምክክር ሥርዓቱ ሲቀረጽም የማኅበረሰቡን የዘመናት የመደማመጥ፣ የእርቅ እና የይቅርታ እሴቶችን እንደመሠረት ተጠቅሟል ነበር ያሉት። የትኛውንም ልዩነት በኃይል ሳይኾን በውይይት እና በሃሳብ የበላይነት ተደማምጦ የመፍታት፤ ያለፈውን ቁስል አክሞ ለነገዋ ሀገር በጋራ መቆም እና የኢትዮጵያን ችግሮች በራሷ ልጆች በሀገር በቀል ዕውቀት እና ጥበብ በእርቅ በመፍታት ታላቋን ሀገር ለመጪው ትውልድ የማሻገር ዓላማን ሰንቋል።

ዘላቂ ሰላም እና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት አስተማማኙ አማራጭ ተደርጎ በከፍተኛ ትኩረት እየተሠራበት ነው። የትናንቱ የአባቶቻችን ባሕላዊ ሥርዓት ለዛሬው ሀገራዊ ምክክር ትልቅ ጉልበት ነው።

ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ችግር በዘመናዊ የእርቅ መንገድ (በምክክር ኮሚሽን) ፈትታ ሰላም እና እድገቷን አረጋግጣ ለቀጣዩ ትውልድ ትሻገራለች።

#EthiopianNationalDialogue #ሽምግልና #ሀገራዊምክክር #የሰላምጉዞ #ኢትዮጵያ #PeaceBuilding #Ethiopia🕊️🇪🇹

ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ

Previous article“ሠራዊቱ በጸረ ሽምቅ ስምሪት ያስመዘገባቸው ድሎች የተላላኪዎችን አንገት ያስደፋ እና ሰላም ወዳዱን ሕዝብ ያስደሰተ ነው” ሌተናል ጀኔራል መሐመድ ተሰማ
Next article” የሰጣችሁን ጊዜ ያላሳካናቸውን እንድናሳካ፣ ያላደረስነውን ልማት እንድናዳርስ ቃል ኪዳናችንን የምናድስበት ነው” ከንቲባ አዳነች አቤቤ