“ሠራዊቱ በጸረ ሽምቅ ስምሪት ያስመዘገባቸው ድሎች የተላላኪዎችን አንገት ያስደፋ እና ሰላም ወዳዱን ሕዝብ ያስደሰተ ነው” ሌተናል ጀኔራል መሐመድ ተሰማ

9

 

የምሥራቅ እዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል መሐመድ ተሰማ ከኮር አዛዥ ጀኔራል መኮንኖች እና ከእዝ ስታፍ ከፍተኛ መሪዎች ጋር በመኾን አርብ ገበያ (ብራዳማ) ለሚገኙ የሠራዊት ክፍሎች መመሪያ ሰጥተዋል።

የምሥራቅ እዝ አዛዥ ሌተናል ጀኔራል መሐመድ ተሰማ ሠራዊቱ በጸረ ሽምቅ ስምሪት ያስመዘገባቸው ድሎች የተላላኪዎችን አንገት ያስደፋ እና ሰላም ወዳዱን ሕዝብ ያስደሰተ መኾኑን ተናግረዋል።

ሠራዊቱ የተዘጋጀውን አዲስ ዕቅድ ለመተግበር ባደረገው የጸረ ሽምቅ ስልት ጽንፈኛውን በማጥናት ፣ በስውር በመንቀሳቀስ ፣ በመክበብ እና በመደምሰስ ውጤታማ መኾኑን ገልጸዋል።

ይህ ጽንፈኛ የሕዝብ ጠላት ዘራፊ ብቻ ሳይኾን ሀገርን ለውጭ ጠላት አሳልፎ ለመስጠት የተቀጠረ ባንዳ ነው ብለዋል።

የምንዋጋው ጠላት ሀገራችን ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተደራጀ የባዕዳን ተላላኪ ወሮበላ መኾኑን ተገንዝበን፣ የአያቶቻችንን አደራ ጠብቀን ለተከታዩ ትውልድ የተከበረች ኢትዮጵያን ለማስተላለፍ የጀመርነውን የጸረ ሽምቅ ኦፕሬሽን አጠናክረን መቀጠል አለብን ነው ያሉት።

በቅርቡ የተካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ሕዝባችን ሠራዊታችን በሌለባቸው አካባቢዎች ጭምር ከሩቅ ተጉዞ ይመራኛል ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ የመረጠው ለዘላቂ ሰላም ያለውን ጽኑ ዕምነት ለመግለፅ ነው ብለዋል።

እኛ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለመሸራረፍ የሚጥሩ ኀይሎችን ሴራ እና ሕልም እያከሸፍን የሕዝባችንን ሰላም የሚያረጋግጡ ስምሪቶቻችንን በጀግንነት መወጣት ይገባናል ነው ያሉት።

በመድረኩ ላይ የኮር አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል አዲሱ መሐመድ ፣ የኮር አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል መላኩ ገላነህ ፣ የምሥራቅ እዝ ሎጀስቲክስ ኀላፊ ኮሎኔል ንጋቱ አዱኛ ፣ የኮር ምክትል አዛዥ ፣ የክፍለ ጦር አዛዦች እና ሌሎች መሪዎች ተገኝተዋል።

Previous articleበዋትስአፕ ተጠቃሚዎች ላይ ያነጣጠረው ጥቃት፦
Next article✨ “ትውልድ የሚቀባበለው የሰላም ችቦ፤ ከባሕላዊ የግጭት አፈታት እስከ ሀገራዊ ምክክር”