“ያለ አባት ያሳደኳት ልጄ ክብርን አሳየችኝ” የዋንጫ ተሸላሚዋ ተመራቂ ወላጅ እናት

2

 

ደብረ ብርሃን : ሰኔ 21/2018 ዓ.ም.(አሚኮ) 🎓 ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሠለጠናቸውን ተማሪዎችን አስመርቋል።

ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎችም የዋንጫ እና
የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ከፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ጤና ሣይንስ ኮሌጅ የፋርማሲ ትምህርት ክፍል ተመራቂው ብሩክ ደግነት የሜዳልያ እና የዋንጫ አሸናፊ ኾኗል።

ብሩክ ደግነት ከወሰዳቸው አጠቃላይ ኮርሶች 35 ኤ ፕላስ በማምጣት እና 3 ነጥብ 97 ውጤት በማስመዝገብ ነው አሸናፊ መኾን የቻለው።
ተማሪ ብሩክ ለዚህ ውጤቴ ከግል ጥረቴ ባሻገር የቤተሠቦቼ እና የጓደኞቼ ድጋፍ ቀላል የሚባል አልነበረም ብሏል።

ዛሬ ስመረቅ ሀገሬን እና ሕዝቤን በተማርኩት ሙያ ለማገልገል ቃል ገብቻለሁ ያለው ተመራቂው ቃሌን ለመፈጸም ዝግጁ ነኝ ነው ያለው ።

የብሩክ ወላጅ እናት እና አባትም ልጃቸውን በስነ ምግባር እና በዕውቀት ለመቅረፅ የከፈሉት ዋጋ ፍሬ አፍርቶ በማየታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፤ ልጃችን አኩርቶናል ብለዋል።

ከሴት ተመራቂዎች የከፍተኛው ውጤት ባለቤት ደግሞ የማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ተመራቂዋ ትርንጎ ገዛኸኝ ኾናለች።

3 ነጥብ 96 ያስመዘገበችው ውጤት ነው። የክብር ዋንጫውንም ወስዳለች፡፡ ተመራቂዋ ለአላማ መጽናት ከተቻለ ሁሉን ማሳካት ይቻላል፤ ዋንጫውን የግሌ ለማድረግ አልሜ በትጋት ተምሬያለሁ፤ አሳክቼዋለሁም ብላለች።

የትርንጎ ወላጅ እናት እንዥባን ንጉሴ አንድ ብቸኛ ልጄን ያለ አባት ሥራ ሳልመርጥ የቀን ሥራ እየሠራሁ ነው ያሳደኳት ነው ያሉት።

ልጄ አባቷን በማጣቷ እንዳይጎድልባት እና እንዳይከፋት ከራሴ እርሷን አስቀድሜ ለቁም ነገር እንድትበቃልኝ የእናትነትም የአባትነትም ኀላፊነትን ተወጥቻለሁ ብለዋል።

“ያለ አባት በድህነት ያሳደኳት ልጄ ክብርን አሳየችኝ” ነው ያለው።

ሌላኛይቱ የዕለቱ ባለታሪክ ተመራቂ ሄለን ጌታው ናት።
መምህርት ሄለን ጌታው የአርሲ ዩኒቨርሲቲ መምህርት ስትኾን የ2ኛ ዲግሪዋ በቱሪዝም እና ሆስፒታሊቲ የትምህርት መስክ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተመርቃለች።

የመመረቂያ ጽሑፏን አራስ ቤት ኾና መሥራቷን የተናገረችው መምህርት ሄለን ሴትነት፣ እናነት እና የሁለተኛ ዲግሪ ፈተናዎችን ተቋቁሜ በባለቤቴ እና በወላጆቼ እገዛ ለዛሬዋ ቀን በመድረሴ ኩራት ተሰምቶኛል ብላለች።

የአብራኳን ክፋይ ታቅፋ በመመረቅ የምርቃኑ ተጨማሪ ድምቀት ኾናለች።

#አሚኮ_ዜና #ደብረብርሃን_ዩኒቨርሲቲ #ምርቃት2018

ዘጋቢ፦ ሥነ-ጊዮርጊስ ከበደ

Previous articleኢትዮጵያ የተገለጠችበት ደማቅ ብሔራዊ ቀለም!
Next articleሚሊሻ የሕዝብ ዘብ ነው።