ሚሊሻ የሕዝብ ዘብ ነው።

1

 

ከሚሴ: ሰኔ 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ደዋጨፋ ወረዳ የጉላ ክላስተር ቀበሌዎች የሚሊሻ ምረቃ ተካሂዷል።

ዛሬ የተመረቁት የሚሊሻ አባላት በተሰጣቸው ሥልጠና አካባቢያቸውን እና የሕዝባቸውን ደኅንነት ለመጠበቅ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

የሕዝብን ሰላም የሚያውኩ አካላት ላይ አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ የአካባቢያቸውን ሰላም ማረጋገጣቸውንም ገልጸዋል።

የደዋጨፋ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ መሀመድ ጌታቸው የወረዳው ሚሊሻ በሰላም ጊዜ የሚያርስ በችግር ጊዜ ደግሞ ሰላም የሚያስከብር መኾኑን ተናግረዋል። በፈተና የተረጋገጠ የሕዝብ ልጅ ነው ብለዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አህመድ አሊ ሚሊሻ የሕዝብ ዘብ፣ በችግር ጊዜ ጥላ እና የሕዝብ ጋሻ እንደኾነ ጠቁመዋል።

ሰላም የሁሉ ነገር መሠረት መኾኑን ያነሱት ዋና አሥተዳዳሪው የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እና ማኅበረሰቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ለማስቻል የሚሊሻውን ኀይል ማጠናከር ወሳኝ መኾኑን አስገንዝበዋል።

መንግሥት ለሰላም የዘረጋው እጅ እንዳልታጠፈም አንስተዋል። ታጥቀው በጫካ የሚንቀሳቀሱ አካላት ወደሰላም እንዲመጡም ጠይቀዋል።

በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት
የኮማንዶ እና አየርወለድ ክፍለጦር አዛዥ ብርጋዴል ጄኔራል እሸቱ መንግሥቴ ሀገርን ለማጽናት በሚደረገው ትግል ሚሊሻው ድርሻውን እየተወጣ መኾኑን ጠቅሰዋል። በቀጣይም ሚሊሻው የሕዝብ ጋሻ መኾኑን እያስመሰከረ ሊሄድ ይገባል ነው ያሉት።

#አሚኮ_ዜና #የሚሊሻ_ምረቃ_ኦሮሞብሔረሰብ #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ

ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“ያለ አባት ያሳደኳት ልጄ ክብርን አሳየችኝ” የዋንጫ ተሸላሚዋ ተመራቂ ወላጅ እናት