
ደብረ ብርሃን: ሰኔ 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 🎓 ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሠለጠናቸውን ተማሪዎችን አስመርቋል።
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ለ20ኛ ዙር ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 90 ነጥብ 2 በመቶ ያህሉ ብሔራዊ የመውጫ ፈተናን በተሳካ ሁኔታ ማለፋቸው ተገልጿል።
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስማረ መለሠ (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው በዕውቀት፣ በተግባር እና በሥነ-ምግባር የታነጹ ዘመኑን የዋጁ ባለሙያዎችን ለማፍራት ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ዓለም በቴክኖሎጂ እየተመራች መኾኑን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ ተመራቂዎቹ ከዓለም ነባራዊ ሁኔታ ጋር እንዲራመዱ የሚያስችላቸው በቴክኖሎጂ የታገዘ ተግባር ተኮር ሥልጠና መውሰዳቸውን ተናግረዋል። ለዚህም ማረጋገጫው በብሔራዊ የመውጫ ፈተናው የተመዘገበው አስደናቂ ስኬት መኾኑን ገልጸዋል።
በዕለቱ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር እና የዩኒቨርሲቲው የሥራ አመራር ቦርድ አባል መሠረት በቀለ (ዶ.ር) ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የልህቀት ጎዳናን በመከተል እየተጋ የሚገኝ ተግባር ተኮር ተቋም መኾኑን ገልጸዋል።
ዛሬ የተቀበላችሁት ዲግሪ የዓመታት የልፋታችሁ ውጤት ብቻ ሳይኾን ወደ ፊት ለምትገነቧት ሀገር ታላቅ ሀገራዊ አደራ ማረጋገጫ ማሕተም ጭምር ነው ብለዋል።
📜 በዛሬው የምርቃት ሥነ-ሥርዓት ላይ ከመደበኛ ተመራቂዎች በተጨማሪ፣ በዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢና በመሃል ሜዳ ካምፓስ በከፍተኛ ዲፕሎማ (HDP) እና በእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያ ሥልጠና የወሰዱ 639 መምህራን ሥልጠናቸውን አጠናቅቀው የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል።
#አሚኮ_ዜና #ደብረብርሃን_ዩኒቨርሲቲ #ምርቃት2018
ዘጋቢ፦ ሥነ-ጊዮርጊስ ከበደ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
