
ባሕር ዳር: ሰኔ 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአፋር ክልል ከተሞች የኮሪደር ልማት እየተተገበረ ነው።
መንግሥት በልዩ ትኩረት እና ቁርጠኝነት እያከናወናቸው ካሉ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች መካከል የተቀናጁ የልማት ሥራዎችን በውስጡ ያካተተው የኮሪደር ልማት አንደኛው ነው። ይህ የኮሪደር ልማት የወደፊቱን የከተሞች ገጽታ እና የነዋሪዎችን የኑሮ ጥራት በአዲስ መልክ እየቀረጸ የሚገኝ ሀገራዊ ንቅናቄ ነው።
ይህ ልማት ተራ የመንገድ ማስፋፋት ወይም የጌጣጌጥ ሥራ ሳይኾን የከተማን ምህዳር፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን እና የማኅበረሰብን ሁለንተናዊ መስተጋብር በአንድነት የሚያዘምን የተቀናጀ የከተማ ፕላን ትግበራ ነው።
በአዲስ አበባ ተጀምሮ አስደናቂ ስኬት ያስመዘገበው ይህ የኮሪደር ልማት፣ አሁን ላይ ወደ ክልል ከተሞች በስፋት በመስፋፋት ላይ ይገኛል። የክልል ከተሞች እንደየ አካባቢያቸው ባሕላዊ፤ ታሪካዊ እና መልክዓምድራዊ ሁኔታ ይህንን ልማት በመተግበር ላይ ናቸው።
በአፋር ክልል ዋና ከተማ ሰመራ እና በቅርቡ ደግሞ ደቡብ አፋርን የምታደምቀው አዋሽ ሱባህ ኪሎ ከተማ የብሔራዊ ራዕይ አካል በመኾን የኮሪደር ልማቱን እየተገበሩ ነው።
በሁለቱ ከተሞች የተጀመረው ሥራ በሌሎች የክልሉ ከተሞች ደረጃ በደረጃ ተስፋፍቶ በጥራትና በከፍተኛ ፍጥነት እንደሚቀጥል ተገልጿል።
የክልሉ መንግሥት ሁሉንም ከተሞች ምቹና ዘመናዊ የማድረግ ጽኑ አቋም እንዳላው አስታውቋል። ይህ የኮሪደር ልማት ንቅናቄ በየደረጃው ላሉ የክልሉ ከተሞች አዲስ የተስፋና የዕድገት ብርሃን ይዞ ይሻገራል።
ልማቱ ከተሞች የንግድ፣ የቱሪዝም እና የኢንቨስትመንት መናኸሪያ እንዲኾኑ የሚያደርግ ነው።
የከተሞች የኮሪደር ልማት የነገዋን ዘመናዊት፣ ፅዱ እና ውብ ኢትዮጵያን ለመገንባት ያስችላል።
ከአፋር ክልል ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የኮሪደር ልማቱ የበለጸገች እና ማራኪ አፋርን ለመገንባት በቁርጠኝነት እየተተገበረ ያለ የብልጽግና ደማቅ አሻራ ነው።
