
ባሕር ዳር: ሰኔ 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ለአማራ ክልል ዳኞች እና ለፍትሕ ከፍተኛ እና መካከለኛ መሪዎች ሥልጠና ተሠጥቷል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልሉን የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል እየወሰዳቸው ካሉ ስር ነቀል የለውጥ ሥራዎች አንዱ የዳኞችን፣ የጉባኤ ተሿሚዎችን እና የሠራተኞችን ሙያዊ እና ስነ ምግባራዊ አቅም ማሳደግ ነው።
ሥልጠናውን የሰጡት በፔንስልቫንያ (አሜሪካ) በሚገኘው የኩተዝታውን ዩኒቨርሲቲ የወንጀል ፍትሕ ትምህርት ክፍል ለ27 ዓመታት ያስተማሩት ፕሮፌሰር ፔትሮ ቶጃ የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ካለባቸው ሕዝባዊ አደራ የሚመነጭ ከፍተኛ የኾነ የሙያዊ ስነ ምግባር ባለቤት መኾን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ሕዝባዊ አመኔታን ለማስጠበቅ ሁሉም የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ማኅበረሰባቸውን በላቀ የሙያ ስነ ምግባር ማገልገል ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።
ኀብረተሰቡ በሕይወቱ፣ በንብረቱ እና በነጻነቱ ላይ ወሳኝ አድርጎ የሾማቸው ዳኞች በላቀ የስነ ምግባር ደረጃ ላይ መገኘት አለባቸው ብለዋል። ይሄንን በማረጋገጥ ለሙያቸው ክብር የመቆም ታሪካዊ ሸክም ተጥሎባቸዋል ነው ያሉት።
በአዲስ አባባ ዩኒቨርስቲ ሕግ ትምህርት ቤት መምህር እና ተመራማሪ ዮናስ ተስፋ (ዶ.ር) የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት በችግር ወቅት እና ከችግሩ ማግስት ሕግና ስርዓትን የማስፈን ኀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
በተለያየ ጊዜ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጽናት ለማለፍ የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት ጥንካሬ ወሳኝ ያሉት መምህሩ ተቋማቱ አንዱ ባንዱ ላይ ሳይነሳ፣ ከውድድር በነጻ መንፈስ እና በላቀ ትብብር ሊሠሩ ይገባል ነው ያሉት።
የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት ፈታኝ ሁኔታዎች ባሉበት ወቅትም በሙሉ አቅማቸው ሥራ ላይ ሊኾኑ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ሕገ ወጥነት እንዳይባባስ፣ ሕግ እና ሥርዓት በግለሰቦች እጅ ላይ እንዳይወድቅ፣ ሴቶች እና ሕጻናትን ጨምሮ የንጹሐን መብት እንዳይጣስ የማድረግ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ብለዋል።
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህሩ ሞላልኝ በላይ (ዶ.ር) ተደራሽነትን ለማረጋገጥ አካላዊ መሰረተ ልማት ማሻሻያዎች እና የሥርዓት ማሻሻያዎች ሊደረጉ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሰቲ የፒ.ኤች .ዲ ፕሮግራም አስተባባሪ ዋና ኢንስፔክተር መዳረሻዉ ታፈሰ (ዶ.ር) እና በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሰቲ የሕግ ትምህርት ክፍል ኀላፊ ዋና ኢንስፔክተር ትንሳኤ ገብረክርስቶስ በወንጀል ምርመራ ሂደት ውስጥ የዘርፉ ተቋማት ሊኖራቸው የሚገባውን ኃላፊነት የተመለከተ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው የዲጂታል ፍትሕ አገልግሎት ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ የሚኾንበትን አግባብ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይሠራበታል ብለዋል።
