የጀጎል ዓለም ቅርስ የኮሪደር ልማት ሥራዎች “የወል ትርክት እሳቤዎች” ማሳያ ናቸው – ርእሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

9

 

የጀጎል ዓለም ቅርስ የኮሪደር ልማት ሥራዎች “የወል ትርክት እሳቤዎች” የተግባር ማሳያ መሆናቸውን ርእሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገልጸዋል።

ርእሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ የአራተኛው ዙር የጀጎል ኮሪደር ልማት ሥራዎችን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።

ርእሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ ባለፉት ዓመታት በኮሪደር ልማት ከተማዋን ወደተሻለ ደረጃ የማድረስ፣ቅርሶችን የመንከባከብና የተለያዩ በርካታ ተግባራት ተሠርተዋል።

የኮሪደር ልማት ሥራዎቹ የመደመር መንግሥት ዕይታ ፀጋዎችን እንድንጠቀም አዳዲስ እሳቤዎችን ይዞ የመጣ በመሆኑን ቅርሶችን ከአደጋ የታደገና ሐረርን የቱሪስት መዳረሻነቷን ያጎለበት መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም ለነዋሪውና ለጎብኚው ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ሐረርን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር እንዲጨምር አስተዋጽዎ አበርክቷል ብለዋል።

እንዲሁም የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች “በውስን ሀብትና በውስን ቀናት ጀምሮ መጨረስ” እንደሚቻል ያሳየ ነው ሲሉም አክለዋል።

የልማት ሥራዎቹም እርስ በርስ ከመገፋፋት ይልቅ አብሮነትንና ወንድማማችነትን ያጠናከረ፣ ሕዝብና መንግስትን ያቀራረበ፣ የአይቻልም መንፈስን የሰበረ “የወል ትርክት እሳቤ” ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ ርእሰ መስተዳድር ኦርዲን ገለጻ በክልሉ ከተማና ገጠር ሳቢና ማራኪ አካባቢን የመፍጠር፣ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብቱ እና ኑሮን የሚያሻሽሉ ተግባራት በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የክልሉ ባሕል፣ ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ናስር አህመድ የኮሪደር ልማት ሥራው ለነዋሪውና ለጎብኚዎች ምቹ ከማድረግ ባሻገር ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ መሆኑንም አንስተዋል።

በኮሪደር ልማት ሥራው ውጤታማ ቅንጅታዊ ተሳትፎ የታየበትና አርዓያነት ያለው ተግባር መሆኑን ጠቁመው “ይህም በቀጣይ በምንሠራቸው ሥራዎች ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል” ብለዋል።

በመጨረሻም ርእሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በከተማው ቦቴ፣ ካናል፣ ሕይወት ፋና አዲስ የ18 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራን አስጀምረዋል።

በመርሃ ግብሩ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና የሴክተር መሥሪያ ቤት ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

#አሚኮ #ሐረር #ጀጎል #ኢትዮጵያ

Previous articleበግዕዝ ቋንቋ በሜዳሊያ የተመረቀው የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ አካል ጉዳተኛ ተመራቂ።
Next articleሕጻናት በዕውቀት እና በአስተሳሰብ የበሰሉ እንዲኾኑ መሥራት ይጠበቃል።