ሕጻናት በዕውቀት እና በአስተሳሰብ የበሰሉ እንዲኾኑ መሥራት ይጠበቃል።

11

 

ጎንደር : ሰኔ 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገር ተረካቢ ሕጻናት ደኅንነትን መጠበቅ እንደሚገባ የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታውቋል።

የአፍሪካ ሕጻናት ቀን “የተጠበቁ ሕጻናት ለበለጸገ ትውልድ” በሚል መሪ መልዕክት በጎንደር ከተማ ተከብሯል።

በመርሐ ግብሩ በጎንደር ከተማ የነገ ተስፋ የተቀናጀ በጎ አድራጎት ድርጅት፤ ብሪጅ ማግዳሊን የሕጻናት መንደር እና በጎንደር ከተማ የተገነቡ የሕጻናት መዝናኛ ማዕከላት ተጎብኝተዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዝና ጌታቸው የአፍሪካ የሕጻናት ቀን ሲከበር የሕጻናትን መብት መከበር እና ከጥቃት መጠበቅ መሠረት አድርጎ መኾኑን ገልጸዋል።

ሕጻናት የነገ ሀገር ተረካቢ በመኾናቸው በዕውቀት እና በአስተሳሰብ የበሰሉ እንዲኾኑ መሥራት ይጠበቃል ብለዋል።

የሕጻናት የመማር፣ በሕይወት የመኖር፣ ከአድሎ የነጹ እና የመሳተፍ መብቶቻቸው እንዲከበሩ መሥራት ይጠይቃል ነው ያሉት።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ የሕጻናት መብት እና ደኅንነት ማስጠበቅ ቡድን መሪ ትግስት ገዳሙ በጎንደር ከተማ አሥተዳደር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ሕጻናትን መንግሥት እና መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች እና ማኅበረሰቡን በማሥተባበር ድጋፍ እየተደረገ መኾኑን ተናግረዋል።

በከተማ አሥተዳደሩ የሚገኙ የሕጻናት በጎ አድራጎት ድርጅቶች በከተማዋ ለሚገኙ ሕጻናት እገዛ በማድረግ በኩል ሚናቸውን እየተወጡ መኾኑን ገልጸዋል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ፓሊስ መምሪያ የሴቶች እና ሕጻናት ምርመራ ክፍል ኀላፊ ኮማንደር ፍትፍት አምሳሉ በሕጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል ቀድሞ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

የፖሊስ ተግባር በሕጻናት ላይ ቀድሞ ከመከላከል ጀምሮ ጥቃት ሲደርስም ለፍትሕ እንዲቀርብ ማድረግ ነው ብለዋል።

ሕጻናት ላይ መሥራት የነገ ሀገርን መገንባት በመኾኑ የሃይማኖት ተቋማት በትኩረት ሊሠሩ ይገባልም ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ደስታ ካሣ

Previous articleየጀጎል ዓለም ቅርስ የኮሪደር ልማት ሥራዎች “የወል ትርክት እሳቤዎች” ማሳያ ናቸው – ርእሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ